
በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል ያለው ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ለዘመናት በዓባይ ወንዝ ጂኦፖለቲካዊ የበላይነት እና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ዙሪያ የተቃኘ ነው።
ግብጽ ኢትዮጵያ በውስጥ ችግሮቿ ታስራ እና ተዳክማ እንድትኖር ከወታደራዊ ወረራ እስከ ረቀቀ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሠርታለች።
በታሪክ አጋጣሚዎች እንደሚያሳዩት ግብጽ የዓባይ ወንዝ ምንጭ የኾነችውን ኢትዮጵያን በቁጥጥር ስር ለማዋል ወይም ደግሞ እንዳታድግ እና እንዳትረጋጋ ለማድረግ በርካታ ስልቶችን ተጥቅማለች።
በኬዲቭ እስማኤል ዘመነ መንግሥት ግብጽ የዓባይን ተፋሰስ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል በኢትዮጵያ ላይ ግልጽ ወረራ መፈጸሟን ታሪክ ያስረዳል።
የግብጽ ጦር በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ተደራጅቶ ኢትዮጵያን ለመውረር ቢሞክርም፣ በጀግኖች ኢትዮጵያውያን የጉንደት እና የጉራዕ ውጊያዎች አስከፊ ሽንፈት ገጥሞታል።
ግብጽ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የጎሳ፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ልዩነቶችን በመጠቀም ሀገሪቱ በውስጥ ግጭት እንድትጠመድ ያለረፍት ለዘመናት ሥትሠራ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
በተለይም በኤርትራ አማፂያን እና በሌሎች የታጠቁ ቡድኖች ጀርባ የግብጽ ወታደራዊ፣ የገንዘብ እና የዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ታደርግ ነበር።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደተናገሩት ግብጾች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም መጋፋት የጀመሩት ዛሬ አይደለም። ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት እንዳላት መግለጿን ተከትሎ የተለያዩ ወገኖችን በጠላትነት የማስተባበር ሥራዎቿን ቀጥላለች።
የኢትዮጵያን ነፃነት፣ አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ደኅንነትን የሚፈታተኑ ወገኖችን በዲፕሎማሲ፣ በቁሳቁስ እና በወታደራዊ መስክ ሲረዱ መቆየታቸውንም ጠቅሰዋል።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከመውጣቷ በፊት የኤርትራ ኀይሎችን ጨምሮ የኢትዮጵያን ብልጽግና የማይፈልጉ ወገኖችን የማስተባበር፣ የመርዳት እና የመደገፍ ሥራዎችን ሥትሠራ መቆየቷን ገልጸዋል፡፡
በዘመናችን የዓባይ ውኃ አጠቃቀምን እና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ የግብጽ አካሄድ ከቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት ይልቅ ወደ ዲፕሎማሲያዊ አሻጥሮች እና የስውር እጆች ተቀይሯል።
ግብጽ ኢትዮጵያ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብም ኾነ ለሌሎች ትላልቅ የውኃ ልማት ፕሮጀክቶች ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት (እንደ አይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ) ብድር እና እርዳታ እንዳታገኝ ለዘመናት ሥትሠራ ቆይታለች።
ግብጾች በተለያዩ የአረብ ሊግ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረኮች እና በተለያዩ ወዳጅ ሀገራት ዘንድ የኢትዮጵያን ስም ሲያጠለሹ መክረማቸውን የገለጹት አምባሳደር ዲና ይህ አካሄድ ውጤት አላስገኘላቸውም ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የግብጽን ሕልውና ልታጠፋ እንደኾነ አድርጎ የማቅረብ እና የሕዳሴ ግድቡ የቴክኒክ ደኅንነቱ የተጠበቀ አይደለም የሚሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨትም የተንኮል መርዟን ስትረጭ ባጅታለች።
የግብጽ መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት የግድቡን ሂደት ለማደናቀፍ እና ለማፍረስ ወታደራዊ ዝግጅት እና የዛቻ ፖለቲካን ሲያካሂዱም ቆይተዋል።
ኾኖም ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በራስ አቅም በማጠናቀቅ እና ድርድሮችን በሰላማዊ መንገድ በመምራት የመልማት ተፈጥሯዊ መብቷን ማስከበር ችላለች።
ኢትዮጵያውያን በትብብር እና በአንድነት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ማስጠበቅ እና የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ማድረስ እንዳለባቸውም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
