
በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ በመፍታት ለዘላቂ የሀገር ግንባታ መሠረት ለመጣል የሚደረገው የሀገራዊ ምክክር ሂደት በተስፋ የተሞላ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
በሂደቱ ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ጀምሮ በርካታ የምክክር ሀሳቦች ሲዳብሩበት የቆየው ይህ የሀገራዊ ምክክር መድረክ አሁን ላይ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈ የጋራ የመፍትሔ ሀሳብ ማዕከል ኾኗል።
ጉባኤው ከአርሶ እና አርብቶ አደር እስከ ምሁራን፣ ከሴቶች እና ወጣቶች እስከ አካል ጉዳተኞች እና አዛውንቶች፣ ከግለሰብ እስከ ሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች፣ ከሃይማኖት ተቋማት እስከ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ያሳተፈ አካታች ኾኖ በሀሳብ ብዝኃነት በታላቅ ተስፋ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው እየተሳተፉ የሚገኙት ታዋቂው ተመራማሪ ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካርያ ስለ ሀገራዊ ምክክሩ ሲያስረዱ”ለኢትዮጵያ ከምክክር ውጭ ሌላ ዘላቂ መድኃኒት የለም” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብን ከችግር የሚያወጣ ሁሉንም ማኅበረሰብ የሚወክል ምክክር እየተደረገ በመኾኑ ደስ ብሎኛል ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ። የምክክር ሂደቱ ውጤታማ እንደሚኾን ትልቅ ተስፋ እንዳሳደረባቸውም ገልጸዋል።
የምክክር ሀሳቦች ከታች ጀምረው በውይይት እየዳበሩ የመጡ በመኾናቸው ለመጨረሻው የምክክር ጉባኤ ሲቀርቡም አዲስ አይደሉም ነው ያሉት።
ምክክሩ የተሻሉ ሀሳቦችን በማምጣት ለሀገር ግንባታ የሚኾኑ ሀሳቦችን ተመካክሮ መንገድ ማሳየት እና ለመንግሥት ምክረ ሀሳብ የሚቀርብበት ሂደት እንደኾነም ያብራራሉ።
በምክክር ጉባኤው የሚነሱ ሀሳቦች ለመንግሥት ውሳኔ በግብዓትነት የሚቀርቡ ሀሳቦች እንጂ በጉባኤው ተመካካሪዎች የሚወሰኑ ውሳኔዎች እንዳልኾኑም ያስረዳሉ።
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በርካታ የምክክር ሂደቶች ተከናውነዋል የሚሉት ፕሮፌሰሩ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የምክክር ሂደት ከእነዚህ የዓለምአቀፍ ተሞክሮዎች የተቀመረ በመኾኑ ተምሳሌት እንደሚኾንም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
