
የውጭ እርዳታ ጥገኝነትን በማስቀረት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ሳይታረሱ የቆዩ መሬቶችን በምርት ከመሸፈን ባሻገር፣ የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ በማሠባሠብ የውስጥ አቅምን የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አጉማሴ አንተነህ እንደገለጹት የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሀገርን ክብር ማስጠበቅ በመኾኑ በዞኑ እስካሁን ከ202 ሄክታር በላይ ሳይለሙ የቆዩ መሬቶች በሰብል ተሸፍነዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በችግር ውስጥ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በራስ አቅም ለመደገፍ ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ እና ከ1ሺህ ኩንታል በላይ እህል የተሠበሠበ ሲኾን በሁሉም ወረዳዎች ለአደጋ ጊዜ መከላከያ የሚያገለግሉ የእህል ማከማቻ መጋዘኖች ተዘጋጅተዋ።
በተመሳሳይ በቡሬ ዙሪያ ወረዳ ከአስተራረስ ባሻገር ኅብረተሰቡን በገንዘብ እና በዓይነት በማሳተፍ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በራስ አቅም ለመደገፍ እየተሠራ መኾኑን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙላት አዲስ ገልጸዋል።
በዚህም በወረዳው ፆም ያድሩ የነበሩ ከ31 ሄክታር በላይ መሬቶች በሰብል እንዲሸፈኑ ተደርጓል ነው ያሉት።
በወረዳው የአለፋ ባሲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አንሙት ስንቄ እና አርሶአደር ሙሉነህ ሞሴ በበኩላቸው ያልታረሱ መሬቶችን በሰብል የመሸፈን ሥራ ላይ መሳተፋቸውን እና የገንዘብ እንዲሁም የእህል አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
አክለውም የተዘራውን ሰብል በክትትል እና እንክብካቤ ለተሻለ ምርት ለማብቃት ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ንጉስ ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
