የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለተደራጁ የብሎክ እጣ የማውጣት መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር መሬት መምሪያ ኀላፊ መልካም ሥራ ካሳው ከተማ አሥተዳደሩ በአራት ሳይቶች ማለትም ወረብ፣ አዲስ ዓለም፣ መኮድ እና ሰልቸን ቦታዎች ለመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
901 ማኅበራት እና በዚህ ውስጥ የተደራጁ 19 ሺህ 698 አባላት የሳይት እና የብሎክ ዕጣ እንደሚያወጡም ተናግረዋል።
ለማኅበራቱ በ1 ሺህ 45 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ለመኖሪያ ቤት ተነሽ ለኾኑ 2 ሺህ 225 አርሶ አደሮች ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ የመክፈል ሥራ መከናወኑን አንስተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የመኖሪያ ቤት ማደራጀት ተከልክሎ እንደነበር አስታውሰዋል። ብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር ተግባር የሚያከናውን በኾኑ ክልከላውን በማንሳት ነዋሪዎች እንዲደራጁ እና ቦታ እንዲያገኙ ተሠርቷል ብለዋል።
ከ26 ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች መመዝገባቸውን ነው የተናገሩት። ከዚህ ውስጥ ትክክለኛ መረጃን ያቀረቡ 19 ሺህ 698 ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።
በቴክኖሎጅ የታገዘ ተደጋጋሚ የማጣራት ሥራ በማከናወን 5 ሺህ 772 የመኖሪያ ፈላጊዎች ትክክለኛ መረጃ የሌላቸው እና ለማጭበርበር በመሞከራቸው እንዲቀነሱ ተደርጓል ነው ያሉት።
1 ሺህ 325 ሰዎች በቅሬታ መልስ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ተነሽ ከኾኑ ከ2 ሺህ 225 አርሶ አደሮች ውስጥ 1 ሺህ 704 አርሶ አደሮች 500 ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ይሰጣቸዋል ነው ያሉት። በማጣራት የአርሶ አደሮች ልጆች 150 ካሬ ሜትር ቦታ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።
በዘላቂነት ራሳቸውን እንዲያደራጁ እና ቤተሰቦቻቸውን እንዲያግዙ ይሠራል ብለዋል። “ቅድመ ክፍያውን ወደ ካሳ የቀየርነው የማኅበረሰቡን ችግር በመረዳት የቤት ባለቤት እንድትኾኑ ነው” ሲሉም አንስተዋል።
በቀጣይ 67 የቤት ማኅበራትን ለማጣራት እና ቦታ ለመሥጠት እየተሠራ ነው ብለዋል። በቅርቡ አዲስ ማኅበራትን በማደራጀት ቦታ ለመሥጠት እንደሚሠራም ገልጸዋል። ባልተገባ መንገድ እና በማጭበርበር ቦታ ለማግኘት የሚሞክሩ ግለሰቦችን የመቆጣጠር እና ተጠያቂ የማድረግ ተግባር እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
“ሠርታችሁ እንድትኖሩበት እና ወልዳችሁ እንድትስሙበት እንጅ እንድትሸጡት የመኖሪያ ቦታ አልሠጠንም እና አደራችሁን ተወጡ” ብለዋል።
የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) በክልሉ ከ 2006 እስከ 2018 ዓ.ም 12 ሺህ 673 ነጥብ 70 ሄክታር መሬት ለማኅበረሰቡ የመኖሪያ መሥሪያ ቦታ መሰጠቱን ገልጸዋል። 307 ሺህ 270 ሰዎችም ተጠቃሚ መኾናቸውን አንስተዋል።
በክልሉ በአማካኝ በየዓመቱ 974 ነጥብ 9 ሄክታር መሬት ለመኖሪያ ቦታ እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት።
መንግሥት የቤት ልማት ፖሊሲን በማውጣት ማኅበረሰቡ የቤት ልማት ተጠቃሚ እንዲኾን እየሠራ ነው ብለዋል። ቁጠባን አጠናክሮ በመቀጠል፤ የከተሞችን የገቢ አቅም በማሳደግ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት፤ የቤት ግንባታ በፍጥነት እንዲጀመር በማድረግ እና የልማት ተነሺዎችም በሚያገኙት ካሳ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማገዝ በቀጣይ ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር መኾኑንም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
