
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከቢሊዮኖች በላይ ችግኞችን በመትከል ምድርን የማልበስ ግዙፍ ሀገራዊ ጥረት ብቻ አይደለም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የኾኑ ሕንዳዊት የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች እና የሥነ-ምኅዳር ፈላስፋ ቫንዳና ሺቫ (ዶ.ር) ‘የምድር ዴሞክራሲ’ እሳቤ በጥልቀት ሲቃኝ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን የተበጠሰ ቁርኝት መልሶ የሚጠግንበት ጉዞ ኾኖ እናገኘዋለን። ዶክተር ቫንዳና ሺቫ ምድር የሁሉም ሕያዋን ፍጥረታት የጋራ መኖሪያ መኾኗን እና እያንዳንዱ ፍጡር የመኖር እና የማደግ እኩል መብት እንዳለው ያምናሉ።
በዶክተር ቫንዳና ሺቫ እሳቤ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ዜጎች ተፈጥሮን በመንከባከብ እና በማልማት ሂደት ውስጥ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የምድርን ደኅንነት የማረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ኀላፊነታቸውን እንዴት እየተወጡ እንደኾነ በግልጽ የሚያሳይ ነው። የምድር ዴሞክራሲ አንዱ እና ዋነኛው ምሰሶ ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ አንድ ቤተሰብ መኾናቸውን መቀበል ነው። ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ ክረምት ሲገባ በኅብረት ወጥተው ችግኞችን ሲተክሉ፣ የሚያከናውኑት ተግባር መሬት ላይ ጉድጓድ ቆፍሮ ተክልን ማኖር ብቻ ሳይኾን ከምድር ሥነ-ምኅዳር ጋር ያላቸውን ጥልቅ የደም ትስስር ማደስ ነው።
አፈሩ እንዳይሸረሸር፣ ምንጮች እንዳይደርቁ እና አየሩ እንዳይበከል የሚደረገው ርብርብ ነው። ይህም ዶክተር ሺቫ እንደሚሉት ተፈጥሮ የራሷ የኾነ ውስጣዊ መብት እንዳላት ዕውቅና የመስጠት ትልቅ ማሳያ ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ሀገራዊ ገጽታዋን አረንጓዴ ከማልበስ ባለፈ ለምድር ሥነ-ምኅዳር ሚዛን የመጠበቅ ዓለም አቀፋዊ አስተዋጽኦ እያበረከተች ትገኛለች።
ዶክተር ቫንዳና ሺቫ የምድር ዴሞክራሲ ከታች ወደ ላይ በሚሄድ የሕዝብ ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ መኾን እንዳለበት አጥብቀው ይሞግታሉ።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ስኬት ሚስጥርም ያለው እዚህ ላይ ነው ተብሎ ይታመናል። ይህ ጉዞ በጣት የሚቆጠሩ ባለሙያዎች ወይም ፖለቲከኞች ብቻ የሚመሩት ሳይኾን አርሶ አደሮች፣ ተማሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኛው፣ ወጣቱ እና አረጋዊው ሳይቀር በየአካባቢው የራሱን አሻራ የሚያኖርበት ሕያው የሕዝብ ንቅናቄ ነው። ሁሉ አቀፍ ተሳትፎው ሥነ-ምኅዳራዊ ውሳኔዎችን እና የተፈጥሮ ጥበቃን ወደ ተራው ማኅበረሰብ እጅ በማስገባት እያንዳንዱ ዜጋ የራሱ አካባቢ እና የተፈጥሮ ሀብት ጠባቂ እና ባለቤት እንዲኾን አስችሏል።
ወደ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ምኅዳራዊ ፍትሕ ስንመጣ ደግሞ የምድር ዴሞክራሲ የብዝኃ-ሕይወት ጥበቃን እና የምግብ ሉዓላዊነትን አጥብቆ ይደግፋል። የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በሂደት እያደገ መጥቶ የፍራፍሬ ችግኞችን (እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ቡና) በስፋት ማካተቱ የዚህ ፍልስፍና ተግባራዊ መገለጫ ነው። ይህ እርምጃ የተራቆቱ መሬቶችን ከማገገም ባለፈ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ እና የኢኮኖሚ አቅምን በመገንባት ሥነ-ምኅዳራዊ ጥበቃን ከሰብአዊ ደኅንነት ጋር አስተሳስሮታል።
ዶክተር ሺቫ የተፈጥሮን ዘር አንድ ዓይነት ብቻ ከማድረግ ይልቅ የዝርያዎችን ልዩነት አጥብቀው እንደሚደግፉ ሁሉ ኢትዮጵያም የተለያዩ ሀገር በቀል እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ዛፎች በማቀናጀት የብዝኃ-ሕይወት ሚዛንን እየጠበቀች ትገኛለች።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ ጉዞ የዛፍ ተከላ ዘመቻ ሳይኾን ምድርን የማዳን፣ የኅብረተሰብን አብሮነት የማጠናከር እና ትውልድ ተሻጋሪ ሥነ-ምኅዳራዊ ፍትሕን የማስፈን ጥልቅ የጥበብ መንገድ ኾኖ እናገኘዋለን። ይህ ስኬታማ ጉዞ ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ጋር በሰላም አብሮ የመኖርን የሞራል ልዕልና ለተቀረው ዓለም በተግባር ያሳየችበት እና የሰው ልጅ የጥፋት ሳይኾን የልማት እና የእንክብካቤ ምንጭ መኾን እንደሚችል ያረጋገጠችበት ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
