
ቡሄ ደርሷል! በዓሉን ለምታከብሩ ሁሉ እንኳን አደረሳችሁ። የክረምቱ ቁር እየተሰበረ፣ የፀሐይ ብርሃን መሬቱን ዳግም ማሞቅ ሲጀምር፤ የኢትዮጵያዊነት ማኅበራዊ ትስስር፣ ጥበብ እና የመንፈሳዊነት ኅብረ ቀለም የኾነው የቡሄ በዓል ሀገረኛ ድምቀቱን ተላብሶ ውብ መልክ እና ማራኪ ይዘቱን ይዞ ብቅ ይላል። ይህ በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር ባሕላዊ ትውፊቱ ጥልቅ ነው።
የቡሄ በዓል የክረምቱን መከራ በፈገግታ እና በዘፈን አሸንፎ፣ ወደ ብርሃናማው የመስከረም ወር መሸጋገሪያ የዘመናት ድልድይ ነው። በዚህ ወቅት ዛሬም እንደ ቀድሞው ወጣቶች በደስታ፣ ሕጻናት በሆታ፣ እናቶች በዕልልታ፣ አዛውንቶች በምረቃ ይህንን ታላቅ የባሕላዊ እሴት ካባ በድምቀት ይከናነቡታል። ታዲያ ይህ በዓል በየዓመቱ ነሐሴ13 ቀን በተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት ይከበራል።
በደብረ ታብር ከተማ ደግሞ በልዩ ድምቀት እና ክዋኔዎች ይከበራል። የከተማ አሥተዳደሩ ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አለበል ደመላሽ ክረምቱ ሲሸኝ ከሚከወኑ በዓላት መካከል ቡሄ (ደብረ ታቦር ) አንዱ ነው ብለዋል።
በዚህ በዓል ወጣቶች እና ልጆች ሙልሙል ዳቦ ለመቀበል በየደጁ እየዞሩ በግጥም እና በዜማ የሚያወድሱበት ባሕላዊ ክዋኔዎች አንዱ ነው። ከዕለቱ መግቢያ ጀምሮ ከበሮ እየተመታ በዜማ እና በግጥም የታጀበው የልጆች እና ወጣቶች የ”ሆያ ሆዬ” ጨዋታ ሰፈሩን የደስታ ድባብ ያለብሰዋል።
“ሆያ ሆዬ ሆ በሉ… ማር ከቀዳሁ ወለላ… የብርሃን ጮራ መጣ በሉ” እያሉ ያዜማሉ።
እንዲሁም
መጣና በዓመቱ
ኸረ እንደምን ሰነበቱ
ክፈት በለው በሩን የጌታዬን
ሆያ ሆዬ ሆ! ሆያ ሆዬ ሆ!.በማለት እያዜሙ ይቀባበላሉ።
የሠፈር ልጆች በየቤቱ እየዞሩ ሆያ ሆዬ! እያሉ ይጨፍራሉ። ሙልሙል ዳቦ ይቀበላሉ። በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ ይሰጧቸውና እየገመጡ ጅራፋቸውን ሲያጮሁ ያመሻሉ። የቡሄ ዕለት ለእያንዳንዱ የቤተሰብ እና የዘመድ አዝማድ ልጅ አንዳንድ ሙልሙል ዳቦ በልጆቹ ልክ ይሰጣል።
ልጆቹም ሆያ ሆዬ እያሉ የሚያሰሙት ዝማሬዎች ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ፣ ሰውን የሚያወድሱ እና የሕዝብን ሥነ-ልቦና የሚያንጸባርቁ ናቸው።
ሌላኛው ከወንዶች ልጆች እና ወጣቶች እጅ የማይለየው ጅራፍ ነው። የክረምቱ ጨለማ እና መጥፎ መንፈስ እንዲገፈፍ እንዲሁም የብርሃኑ መምጣት በታላቅ ድምጽ እንዲታወጅ በማድረግ በሰፈሩ ውስጥ ልዩ የደስታ እና የዝግጅት ስሜትን የሚፈጥር የጅራፍ ማጮህ ባሕላዊ ክዋኔ ያከናውናሉ።
የችቦ ብርሃን እና የክረምት ሽኝት አብሮ የማይለየው ክዋኔ ነው። የቡሄ ማታ ላይ የሚለኮሰው ችቦ የክረምቱ ግዝፈት እየተገፈፈ ወደ ብርሃናማው ዘመን መሸጋገሩን ያበስራል። ሕጻናት እና ጎልማሶች ችቦውን አብርተው ሲዘዋወሩ የመንደሮቹን ውበት እና ድምቀት ያሳምሩታል።
ታዲያ ሙልሙል ዳቦም የአብሮነት ማዕድ መገለጫ ነው።
እናቶች ለልጆች የሚኾን ልዩ ባሕላዊ ዳቦ (ሙልሙል ዳቦ) በማዘጋጀት ለምሥጋና የመጡ ልጆችን ያስተናግዳሉ። ይህ ማዕድ የማካፈል ባሕል በጎረቤቶች መካከል ያለውን ፍቅር፣ መተሳሰብ እና የእንግዳ ተቀባይነት እሴት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያሸጋግር እሴት ነው።
ቡሄ የሰማይ መጋረጃ ተገልጦ የከዋክብት እልልታ ይሰማል። ወጣቶች ጅራፋቸውን ሲያጮሁ የምድር ሐዘን ተገፎ ብርሃን ይወለዳል፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ የቡሄ ዜማ ከየቤቱ ይደገሳል በየሰፈሩ ይደምቃል።
ኀላፊው እንደተናገሩት ይህን ባሕል ባሕላዊ ይዘቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍም በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
