የሀሳብ አውድማ እና የምክክር ሸማ፦ የሀሳብ ገበያ ከሚፈጥረው እውነት የሚፈነጥቀው ሀገራዊ ንጋት

9
✨የሰው ልጅ ማኅበራዊ ፍጡር ነው። ከሌሎች ፍጡራን የላቀ የሚያደርገው ግን የአመክንዮ፣ የምክንያታዊነት እና የሀሳብ ልውውጥ አቅሙ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በሰሞኑ መግለጫቸው “በሀሳብ ላይ ከመመካከር እና ከመከራከር ባለፈ ሀሳብ ያቀረበን አካል ማሸማቀቅ በፍጹም አይፈቀድም” ብለዋል። ይህም ማኅበረሰቡ ከግጭት እና ከመጠፋፋት አዙሪት ወጥቶ በሠለጠነ መንገድ ልዩነቶችን የሚያስታርቅበትን የጠለቀ መንገድ የሚነግር ነው።
ሀሳቦች በሠለጠነ አውድማ ሲፋጩ እውነት ትጠራለች፤ አንዱ የሌላውን መነጽር ተውሶ የችግሩን ሥረ-መሰረት ማየት ሲጀምር ደግሞ የጠነከረ የጋራ መግባባት ድልድይ ይገነባል። ይህ አገላለጽ ጉልበት እና ኅይልን በምክንያታዊነት እና በውይይት በመተካት ዴሞክራሲያዊ እና የሠለጠነ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚያስፈልገውን መሰረታዊ ምሰሶ በግልጽ የሚያስገነዝብ ነው።
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ዘመናትን የተሻገሩ እና እጅግ ውስብስብ የኾኑ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ታሪካዊ ቅራኔዎችን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይትን ባሕል በማድረግ ብቻ ነው። ለዚህም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሒደት አስረጂ ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ ልሂቃን የድርድር መድረክ ብቻ ሳይኾን የሕዝብ ብሶት፣ ስጋት፣ ፍላጎት እና ተስፋ በነጻነት የሚንሸራሸርበት፤ አድማጭ እና ተደማጭ የሚገናኙበት ታላቅ የሀሳብ ገበያም ነው። በዚህ ሒደት ውስጥ መከራከር መጣላት አለመኾኑን፣ መመካከርም መሸነፍ ሳይኾን የጋራ ሀገራዊ ድልን ማለም እንደኾነ በተግባር ማሳየት የዘመኑ የሠለጠነ ፖለቲካ ትልቁ መገለጫ ነው።
የሀሳብ ልዕልናን በማክበር እና የታጋሽነት መርኾዎችን በመከተል የሚደረግ ማንኛውም ሀገራዊ ጉዞ እጅግ ፈታኝ እና ጊዜን የሚጠይቅ ነው። በመጨረሻ የሚያስገኘው ዘላቂ ሰላም እና ሀገራዊ መግባባት ደግሞ በዋጋ የሚተመን አይደለም።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው የምክክር ሒደት በጥርጣሬ፣ በመፈራራት እና በመጠለፍ ታጥሮ የቆየውን የፖለቲካ ባሕል በግልጽነት፣ በመከባበር እና በመደማመጥ ለመተካት የተወጠነ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው ተብሎ ይወደሳል። ይህ እርምጃ ልዩነቶችን እንደ ጸጋ በመቀበል ሀገርን ከማፍረስ አደጋ ታድጎ በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም፣ የዜጎችን እኩልነት እና አብሮነት ለማረጋገጥ የሚደረግ የብስለት እና የሠለጠነ ማኅበረሰብ የእርምጃ መጀመሪያ ተደርጎም ሊወሰድ ይገባዋል።
✍️ በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ያስተላለፉት መልእክት፦
Next articleየከተሞችን ልማት ለማፋጠን እና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ከተሞች በፕላን ሊመሩ ይገባል።