
የአማራ ክልል ፕላን ኢንስቲትዩት የምሥራቅ ጎጃም ዞን የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እና የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር መሪዎች እና ባለሙያዎች በተገኙበት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ እንዲሁም በተለዩ የሕግ ማዕቀፎች ላይ የሥልጠና መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ፕላን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ምትኩ ዓለማየሁ (ዶ.ር) የከተሞችን ልማት ለማፋጠን እና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ከተሞች በፕላን ሊመሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
አካታች የኾነ ፕላን ለማዘጋጀት የነዋሪዎችን፣ የመንግሥት አካላትን እና የባለሙያዎችን የተቀናጀ ተሳትፎ እንደሚስፈልግም አመላክተዋል፡፡
የከተማ እና የገጠር ቀበሌ ማዕከላትን ፕላን ማዘጋጀት፣ የተሠሩ ፕላኖችን መተግበር፣ በከተሞች የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን ማከናወን፣ በመረጃ ማዕከልነት ማገልገል እና ተግባራትን የኅብረተሰብ ተሳትፎን ባረጋገጠ መልኩ መፈጸም ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመለት ዓላማ አንጻር የሚፈጽማቸው ቁልፍ ተግባራት ስለመኾናቸውም አመላክተዋል፡፡
መዋቅራዊ እና ስትራቴጂክ ፕላኖችን ጨምሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 137 ፕላኖች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በፕላን ዝግጅት እና ትግበራ ሂደቱ ከ14 ሺህ በላይ ዜጎችን ማሳተፍ እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት የ69 ከተሞችን ፕላን በማጽደቅ ወደ ተግባር እንዲገቡ ተደርጓል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።
የ50 ከተሞች ፕላን ክትትል እና ከ31ሺህ በላይ የፕላን ስምምነቶችን በመስጠት ከተሞች ወደ ልማት እንዲገቡ ስለመደረጉም አብራርተዋል፡፡በተያዘው በጀት ዓመትም 137 የገጠር ቀበሌ ማዕከላት እና የ50 ታዳጊ ከተሞችን ፕላን ለማዘጋጀት በትኩረት ይሠራልም ብለዋል፡፡
ከተሞች ለሚዘጋጅላቸው ፕላን በራሳቸው አቅም ወጭን መሸፈን ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የዜጎችን መብት እና ፍላጎት በማስጠበቅ ጊዜውን የዋጁ እንዲኾኑ ለማስቻል ከተሞች በፕላን እንዲመሩ ለማድረግ ወደ ተግባር መገባቱን የገለጹት ደግሞ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ ናቸው፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ፕላን ለከተማ ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ ሚና ያለው መኾኑን አንስተዋል፡፡በፕላን ላይ የሚፈጸሙ ጥሰቶች ለከተሞች ማነቆ ናቸው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከፕላን ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከክልሉ ፕላን ኢንስቲትዩት ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
የመድረኩ ተሳፊዎች በበኩላቸው ከተሞች ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በፕላን እንዲመሩ እና ዜጎች የሚገባቸውን አገልግሎት በተሳለጠ መልኩ እንዲያገኙ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡በቀጣይ በባሕርዳር እና በጎርንደር ከተሞች መሰል መድረኮች እንደሚካሄዱ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
