የባሕር በር ጉዳይ ቅንጦት ወይስ ሕልውና?

18
ኢትዮጵያ በባሕር በር እጦት ምክንያት እጆቿን አሳስራ በመቀመጥ የሌሎች ሀገራትን መልካም ፈቃድ ብቻ እንድትጠብቅ ተደርጋለች። ለወደብ ኪራይ ረብጣ ገንዘብን እንድትከፍል፤ ዕድገቷ የቁልቁለት ጉዞ እንዲኾን፤ ወጣቶቿ በወደብ ዙሪያ የሥራ ዕድል እንዳይፈጠርላቸው በማድረግም የበይ ተመልካች እንድትኾን የማድረግ ሥራ ገቢራዊ ኾኗል።
የባሕር በር ጉዳይ ከኢኮኖሚ ባሻገር ሀገር ሉዓላዊነቷን እና ብሔራዊ ደኅንነቷን እንዳታስጠብቅ እንቅፋት የሚፈጥር ነው። የባሕር በር የሌላት ሀገር ደኅንነቷ በአስተማማኝ ሁኔታ ባለመጠበቅ በጠላቶቿ ጥቃት እንድትጋለጥ የሚያደርግ መኾኑን ምሁራን ይገልጻሉ።
የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ እንዳለ ንጉሤ የባሕር በር ጉዳይ ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጡት ልዩ ፍላጎት ነው ይላሉ።
የባሕር በር ከደኅንነት፤ ከነጻነት፤ ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና ከዓለም ከአቀፍ ግንኙነት ጋር ቁርኝነት ያለው መኾኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ምሳሌ መኾኗ፤ በወቅቱ የነበራት የግዛት ስፋት እና ቀድማ መሠልጠኗ በቀኝ ግዛት ያልተሳካላቸው ሀገራት ኢትዮጵያን ከባሕር በር እንድትገለል አድርጓል ነው ያሉት።
የግብጽ መንግሥት እና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመኾን ከሕግ ውጭ ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፍ እይታ ለማራቅ ከባሕር በር እንድትርቅ አድርገዋል ብለዋል።
ይህም በኢኮኖሚ እንድትጎዳ፤ ዕድገቷ የዝቅታ ጉዞ እንዲኾን፤ ሀገር ለዘርፈ ብዙ ጉዳት እንድትጋለጥ አድርጓል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ የገነባችውን ወደብ ማጣቷንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ በመኾኗ የቀጠናውን የባሕር በር ደኅንነት ለማስጠበቅ ትልቅ ሚና እንደሚኖራትም ገልጸዋል። የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የኢኮኖሚ ዘርፉን ለማሳደግ ትልቅ ጥቅም እንዳለውም አንስተዋል። የባሕር በር አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የማይገባ እንደኾነ ነው የተናገሩት። በርካታ የዓለም ሀገራት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እየደገፉ መኾኑንም አንስተዋል።
የታሪክ ተመራማሪው እና የፖለቲካ ተንታኙ ኢብራሂም ሙሉሽዋ (ዶ.ር) በታሪክ ቀይ ባሕር የሌለበት ኢትዮጵያ ሥልጣኔ የለም ብለዋል። ዓለም የኢትዮጵያ ታሪክን በማወቁ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል እንድትኾን በወቅቱ መወሰኑን ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሕልውና ጉዳይ እንጅ የቅንጦት አለመኾኑንም ጠቅሰዋል። የዲፕሎማሲያዊ ጫና በመፍጠር፤ የዓለም ሀገራት የኢትዮጵያን ጥያቄ እንዲረዱት በማድረግ የባሕር በር ተጠቃሚ እንድትኾን መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
እናም የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በአንድነት መቆም እና በኅብረት መታገል ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየታሪክ እስረኝነት እና የዘመን ማዕበል፦ ከእውነታው የተፋታ ያረጀ የፖለቲካ ግርዶሽ !
Next articleአፈር እና ውኃን ያስታረቀው የወጣት ጋሻው ተሞክሮ