የታሪክ እስረኝነት እና የዘመን ማዕበል፦ ከእውነታው የተፋታ ያረጀ የፖለቲካ ግርዶሽ !

2
የፖለቲካ ፍልስፍና እንደ ተፈጥሮ ሕግ ሁሉ የዘመናትን ፍሰት እና የተለዋዋጭ ሁነቶችን ምት አዳምጦ ራስን ማደስን አጥብቆ የሚጠይቅ ሂደት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ዛሬ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሊሳካ በማይችል በአሮጌ የፖለቲካ ሀሳብ እና አመራር ውስጥ ተቀርቅሮ ይገኛል” ብለዋል። ይህ ሀሳብ ጊዜ በለወጠው መድረክ ላይ የትናንትን ተውኔት ለመከወን የሚደረግን አሰልቺ እና ፍሬ አልባ የቡድኑን ሙከራ በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ዓለም እና ኢትዮጵያ በአዲስ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ንቃተ-ህሊና ማዕበል ውስጥ ናቸው፤ ይህ እየኾነ ባለበት በአሁኑ ዘመን ባረጀ እና ጊዜው ባለፈበት የፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ መታጠር፣ ከእውነታው ዓለም ጋር ከመፋታት አልፎ የራስን ፖለቲካ ህልውና በገዛ እጅ ወደ መቃብር የማውረድ ያህል ይቆጠራል ነው ያሉት።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ የትናንቷ አይደለችም፤ የዜጎች የንቃት ደረጃ፤ የጂኦ-ፖለቲካዊ ስብጥሩ፤ የመረጃ ልውውጥ ፍጥነቱ የፈጠረው አዲስ ማኅበረሰብ የቆየውን የመከፋፈል እና የሴራ ፖለቲካ ትርክት ሊሸከም የሚችል ትከሻ የለውም።
በዚህ የብርሃን ፍጥነት በሚጓዝ ዘመን ውስጥ በአሮጌ የፖለቲካ ሀሳብ እና አመራር ውስጥ ተቀርቅሮ መገኘት ማለት በጊዜ ማሽን ወደ ኋላ ተጉዞ የሞተን ታሪክ እንደገና ለማንሠራራት ከሚደረግ ቅዠት የተለየ ትርጉም አይኖረውም ማለት ነው።
አመራሩ ራሱን ካለፈው የትምክህት እና የብቻ ጠቅላይነት አዙሪት መውጣት አለመቻሉ ቡድኑን ከወቅቱ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ሪትም ጋር እጅግ አራርቆታል።
አንድን የፖለቲካ ኃይል ከውድቀት የሚያድነው የጦር መሳርያ ክምችት ወይም ያለፈ ታሪክ ጉራ ሳይኾን እንደ ዘመኑ እውቀት ራስን የማደስ ብቃት እና የተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ንባብ በትክክል መተንተን መቻሉ ነው ይላሉ ዓለም አቀፍ ምሁራን።
የፖለቲካ መሪነት ጥበብ የትናንትን ክብር ማውሳት ብቻ ሳይኾን የነገን ራዕይ መቅረጽ ጭምር መኾን ይገባዋል። የድሮውን የፖለቲካ ካባ ላለማውለቅ መፍጨርጨር ግን ቡድኑን ከሕዝብ እውነተኛ ፍላጎት የነጠለ እና በፖለቲካዊ የክስረት ጎዳና ላይ ያቆመ የታሪክ እስረኛ አድርጎታል።
ከጊዜው ጋር አብሮ የማይራመድ ማንኛውም አስተሳሰብ የቱንም ያህል በግትርነት ቢታቀፉት ከዘመኑ እውነታ ጋር ተጋጭቶ መፈረካከሱ የማይቀር የተፈጥሮ ሕግ ነው።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ43 ፍርድ ቤቶች የዲጂታላይዜሽን አሠራርን ተግባራዊ እያደረገ ነው።
Next articleየባሕር በር ጉዳይ ቅንጦት ወይስ ሕልውና?