
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2018 በጀት ዓመት የፍርድ ቤቶች የዕቅድ አፈጻጸም እና በ2019 በጀት ዓመት ተግባራት ዙሪያ ከሚመለከታቸው የዘርፉ መሪዎች ጋር እየመከረ ነው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ባለፉት ሦስት ዓመታት የፍትሕ እና የዳኝነት ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል። በዚህም በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
በፍርድ ቤቱ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የዲጂታላይዜሽን ሥርዓት ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን፤ ጊዜን የሚቆጥብ፤ ወጪን የሚቀንስ እና የተገልጋዮችን እንግልት የሚያስቀር አሠራር መኾኑን አብራርተዋል።
በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጅ ዳይሬክተር መኳንንት አገኘሁ (ዶ.ር) በፍርድ ቤቱ የተጀመረው የዲጂታላይዜሽን ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዲጂታላይዜሽን አሠራርን የጀመረው የዲጂታል የመሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት መኾኑንም አብራርተዋል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከወረዳ ፍርድ ቤት እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ የራሱ የኾነ የኔትወርክ ዝርጋታን ማከናወን ችሏል ነው ያሉት።
በመጀመሪያው ዙር በተሠራው የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን 14 የከፍተኛ ፍርድ ቤቶችን እና የባሕር ዳር ማረሚያ ቤትን በኔትወርክ በማስተሳሰር ወደ ዲጂታል ሥርዓት ማስገባት እንደተቻለ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
በሁለተኛ ዙር የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ደግሞ እንደ ክላስተር በሚያገለግሉ 27 የወረዳ ፍርድ ቤቶች ላይ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል። እስከአሁን ድረስ በ43 ፍርድ ቤቶች በኔትዎርክ በማስተሳሰር የዲጂታል ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉንም አብራርተዋል።
የዲጂታል ሥርዓት በመተግበሩ በበጀት ዓመቱ ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ ባለጉዳዮችን ከወጪ ማዳን መቻሉንም አንስተዋል። ፍርድ ቤቱ ደረጃውን የጠበቀ አሠራር እንዲተገብር የዲጂታል አሠራሩ ከፍተኛ መደላድል መፍጠሩንም ጠቁመዋል።
በቀጣይ የ2019 የበጀት ዓመት የተጀመሩትን የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች በሌሎች የወረዳ ፍርድ ቤቶች ለማዳረስ ትኩረት እንደሚደረግ አመላክተዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አየነ ተስፌ ፤ በተጀመረው የዲጂታል አሠራር ከዞን የሚነሱ ባለጉዳዮች ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መምጣት ሳይጠበቅባቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ያስቻለ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ ወረዳ ፍርድ ቤቶች መካከልም የወልድያ ከተማ እና የላሊበላ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤቶች የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ተግባራዊ እየተደረገባቸው እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁ
