‎”ለሰላም እና ለዕድገት ዋነኛ መፍትሄ የኾነውን አብሮነትን ባሕል ልናደርግ ይገባል”

3

‎‎የሃይማኖት አባቶች አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

‎የ2019 አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዝዳንት ቄስ ደረጀ ጀምበሩ እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

‎ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው ባሳለፍነው ዓመት የሠራናቸውን መልካም እና መጥፎ ድርጊቶችን በመገምገም ለሰላም እና ለዕድገት ዋነኛ መፍትሄ የኾነውን አብሮነትን ባሕል ልናደርግ ይገባል ብለዋል።

‎ብጹዕነታቸው ሁሉም በአዲስ ዓመት ከልብ በመጸጸት፣ ከመራራቅ እና ከጎጠኝነት በመራቅ መታዘዝን፣ ፍቅርን እና አንድነትን በተጨባጭ ማሳየት ይገባዋል ሲሉ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

‎አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ ለአዲስ ዓላማ በመዘጋጀት መቀበል እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዝዳንት ቄስ ደረጀ ጀምበሩ ናቸው።

‎አዲሱን ዓመት ስንቀበል ካለፉ ስህተቶች በመማር ሰላምን ብቻ በመስበክ በተግባር በይቅርታ መንፈስ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።

‎በአዲሱ ዓመት የሚጎዳን ነገር ሁሉ በማራቅ ለፍቅር፣ ለሰላም እና ለአብሮነት ራስን በማዘጋጀት የጋራ የኾነች ኢትዮጵያን በመገንባት ዓመቱን ልንቀበል ይገባል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ናቸው።

‎የሃይማኖት አባቶች በመልዕክታቸው በአዲሱ ዓመት ዜጎች በየሃይማኖታቸው ለፈጣሪያቸው ተገዥ በመኾን ለሌሎች የመኖር፣ ሀገርን የማሰብ እና የጋራ የኾነ ማንነትን የመገንባት ባሕል ሊያዳብሩ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

‎#አሚኮ #የአዲስ_ዓመት_ምኞት#ኢትዮጵያ🇪🇹

‎#አዲስ_አበባ #ጳጉሜን_05_2018_ዓ_ም

‎ዘጋቢ:- በራሄል ደምሰው

‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article‎”ስኬቶቻችንን የሞራል ስንቅ አድርገን በአዲሱ ዓመት የላቀ ውጤት ለማምጣት በቁጭት እንተጋለን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ