
ወጣት ጋሻው ተሻገር የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ ትልቅ ሕልም ነበረው። ሆኖም በንግድ ዓለም የገጠመው ያልታሰበ ኪሳራ ተስፋ አስቆረጠው። የተሻለ ሕይወትን ፍለጋም የወላጆቹን ፍቅር እና የወጣበትን ቀዬ ተሰናብቶ የጎረቤት ሀገር ሱዳን አፈርን ረገጠ።
በስደት ሀገር ያሳለፈው ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ ሕልሙን ከማክሸፉ ባሻገር ወጣትነቱን በከንቱ አሳለፈበት። ከዚያም በቁጭት እና ትካዜ በተሞላበት የስደት ምድር ውስጥ ሳለ አንድ እውነት አዕምሮው ውስጥ ብልጭ አለ—በዓይነ ሕሊናው የገንዳ ውኃ ወንዝ በከንቱ ሲፈስስ እና የአባቱ ለም መሬት ጾም ሲያድር ታየው።
ይህ የቁጭት ሀሳብም ጋሻውን ከስደት መንገድ መልሶ ከቀዬው ሀብት ጋር ለማስታረቅ ትልቅ ስንቅ ኾነው።
ወጣት ጋሻው እዚያው በሰው ሀገር ጊዜውን እና ጉልበቱን በከንቱ ላያባክን፣ የአባቱን ለም መሬት እና የሚፈሰውን ውኃ በልማት ለማስታረቅ ቃል ገባ።
ጋሻው የተስፋ ስንቁን አዘጋጅቶ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። እጁ ላይ የነበረችው መነሻ ካፒታል 5 ሺህ ብር ብቻ እንደነበረች ከአሚኮ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል። በእሷም አነስተኛ የውኃ ሞተር ፓምፕ እና ምርጥ ዘሮችን በመግዛት የአባቱን ማሳ በቋሚ አትክልት እና ፍራፍሬዎች ማልማት ጀመረ።
ጉዞው ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም። ሥራውን ሲጀምር የአካባቢው ሰው እንደ ሞኝ ይቆጥረው፣ በሥራውም ይሳለቅበት እና ይስቅበት እንደነበር ትውስታውን አጫውቶናል። የባሰበት ደግሞ ሽንኩርት አልምቶ የደረሰበት ከፍተኛ ኪሳራ ነበር። ነገር ግን ተስፋ መቁረጥ ለጋሻው ሁለተኛ አማራጭ አልነበረም። የሰዎችን አሉቧልታ እና የኪሳራውን ሕመም ችሎ ለራሱ ለመለወጥ የገባውን ቃል ለመጠበቅ ወደ ኋላ አላለም።

“አፈር፣ ውኃ፣ ጉልበት፣ ሀሳብ እና ዕውቀት እያለ በሰው ሀገር መሰደድ ወጣትነትን እና ጉልበትን በከንቱ መብላት ነው። ሀገራችን ባላት ጸጋ ሠርተን መለወጥ እየቻልን ራስን ለስደት አሳልፎ መስጠት አላዋቂነት ነው!” ይላል ወጣት ጋሻው።
የጽናት ውጤት አይቀርም እና መጀመሪያ በአባቱ 4 ሄክታር መሬት ላይ የተተከሉት የማንጎ፣ ሎሚ፣ ዘይቶን እና ሌሎች ቋሚ ተክሎች ከዓመታት ድካም በኋላ አብበው ማፍራት ጀመሩ።
ጋሻው ባገኘው ገቢ አልቆመም፤ መሬት ከግለሰቦች እየገዛ የመስኖ ልማቱን ማስፋፋቱን ተያያዘው። ዛሬ ላይ 21 ሄክታር የሚኾን ሰፊ መሬት በቋሚ አትክልት እና ፍራፍሬዎች ሸፍኖ ከተማዋን የምድር ገነት አድርጎታል።
አሁን ላይ ከማሳው በዓመት ከ600 እስከ 700 ኩንታል ማንጎ፣ እስከ 200 ኩንታል ሎሚ እና ብርቱካን በማምረት ወደ አዲስ አበባ ይልካል።
ዛሬ ጋሻው ራሱን እና ቤተሰቡን ከችግር ማውጣት ብቻ ሳይኾን ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ፣ ምርጥ ዘር ለአካባቢው አርሶ አደሮች የሚያከፋፍል እና የአካባቢው ሕዝብ አርዓያ መኾን የቻለ ባለሀብት ኾኗል።
“በኢኮኖሚ የመለወጥ ህልሜ ወሰን አልነበረውም፤ ከስደት ተመልሼ አፈር እና ውኃን አስታርቄ የራሴን እና የቤተሰቤን ሕይወት መቀየር ችያለሁ” ሲልም አጫውቶናል።
“ዛሬ በብዙ ድካም እና ወጪ ያቆምኩት ይህ ልማት ለዛሬዬ ብቻ ሳይኾን ነገ ለልጆቼ የሚሻገር የሕይወት ዘመን በረከት ነው” ሲልም ጋሻው በደስታ እና በእርካታ ተሞልቶ ይናገራል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ1 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በቡና እና በቆላ ፍራፍሬ መሸፈኑን በዞኑ ግብርና መምሪያ የፍራፍሬ እና ቴክኖልጅ ሽግግር ቡድን መሪ አቶ አዲስዓለም ቢተው ተናግረዋል።
በዞኑ ከ25 ሺህ 700 በላይ አልሚዎች እየተሳተፉ ሲኾን በበጀት ዓመቱ ከ140 ሺህ ኩንታል በላይ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት መገኘቱንም ቡድን መሪው አረጋግጠዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ዐውደ ጥናት ላይ እንደገለጹት በኢትዮጵያ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ውስጥ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአንድ ወቅት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የፍራፍሬ እና አትክልት ምርት በተለየ ሁኔታ አጥጋቢ ኾኗል ሲሉ አብራርተዋል።
የጋራ እድገት ለማስገኘት ብሎም የምግብ ዋስትና ትልማችንን አሳክቶ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ላይ ጠንክረን መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የወጣት ጋሻው ተሻገር የሕይወት ጉዞም የሚያስተምረን ትልቅ እውነት አለ። ብዙዎች የወጣትነት ጉልበታቸውን እና ወርቃማ ጊዜያቸውን ባልተረጋገጠ የስደት ጎዳና ላይ ሲያባክኑ ይታያል። ነገር ግን እውነተኛው ሀብት ያለው በሰው ሀገር ምድር ሳይኾን በገዛ ሀገራችን አፈር፣ ውኃ እና ጥረታችን ውስጥ ነው።
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_06_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
