የሕዳሴ ግድቡ ምዕራፍ የተዘጋባት ግብጽ በሌላኛው የሴራ መንገድ ተከስታለች።

12
የኢትዮጵያን ብርቱ የዲፕሎማሲ ክንድ መቋቋም አልቻለችም፤ ከንቱ እብሪቷ ምኞቷን ሊያሳካላት አልቻለም፤ የሃሰት መረጃዎቿም በዓለም አቀፍ ዘንድ ተቀባይነት አላገኙም፤ የሕዳሴ ግድቡ ርሃብ እና ድርቅ ያመጣል በማለት ያሳየችው የአዞ እንባም የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን አላስገረመም፤ የኢትዮጵያ ስኬት፤ ተጠቃሚነት እና የኢኮኖሚ ዕድገት ለግብጽ ታላቅ ሽንፈት ኾኗታል።
ለዘመናት የሕዳሴ ግድቡ እንዳይጠናቀቅ አሲራለች። ኾኖም ግን የተንኮል ሸፍጧ ታላቁ ሕዳሴ ግድብን ከመጠናቀቅ አላገደውም። የኢትዮጵያን ጠንካራ ዲፕሎማሲ መስበር ያልቻለችው ግብጽ ከሰሞኑ ደግሞ ከሱዳን ጋር በመናበብ የውኃ መጠን ቀንሶብኛል በማለት ሌላ ለቅሶን ጀምራለች።
የውኃ ሃብት ተመራማሪ እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዓለምአቀፍ የምሁራን ጥምረት አባል ጥሩሰው አሰፋ (ዶ.ር) ከሰሞኑ ከመገናኛ ብዙኀን ጋር ባደረጉት ቆይታ ከ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ግብጽ ኢትዮጵያ ከዓባይ ወንዝ እንዳትጠቀም ጥረት ስታደርግ መቆየቷን ተናግረዋል።
የዓለም ሀገራት በውኃ እና በተለያዩ ዘርፎች በጋራ በሚሠሩበት ዘመን ግብጽ እኔ ብቻ ተጠቃሚ ልሁን ማለቷ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ጥቅሞቿን ትታ የግብጽን አሳሪ ስምምነት እንድትፈርም፤ ኀይል ብቻ እንድታመነጭ ግብጽ ደግሞ በግብርናው ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትኾን አሳሪ ስምምነትን እያቀረበች መኾኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ሁሉንም በማሸነፍ የዓባይ ግድብን ማጠናቀቋን ገልጸዋል። ከሰሞኑ የግብጽ እና የሱዳን ሚዲያዎች ኢትዮጵያ የውኃ ፍሰቱን እየቀነሰች እንደምትገኝ የሃሰት መረጃዎችን እያሠራጩ መኾኑን ተናግረዋል። ተመራማሪው የሱዳን እና ግብጽ ግድቦች ከዓባይ በሚያገኙት ፍትሐዊ የውኃ ፍሰት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ መኾናቸውን ነው ያነሱት።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውስን አቅም ያላቸው የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ግድቦች በጎርፍ እንዳይጎዱ እንደሚያግዝም ተናግረዋል። ከግድቡ መጠናቀቅ በኋላም የውኃ ፍሰቱ ሳይቀንስ መቀጠሉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ 85 በመቶ የዓባይ ወንዝ ባለቤት ብትኾንም አብሮ መሥራትን አማራጭ በማድረግ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜ በተደረጉ የስምምነት ውይይቶች ላይ መረጃ መለዋወጥን፤ የመረጃ ክትትልን እና አብሮ መሥራትን በማስቀደም መሥራት እንደምትፈልግ ለግብጽ እና ሱዳን በተደጋጋሚ ብታሳውቅም ግብጽ ግን እኔ ብቻ ተጠቃሚ መኾን አለብኝ በማለት ራስ ወዳድ መርህን እየተከተለች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከዝናብ ጥገኝነት ለመውጣት ግድቦችን ማስፋት፣ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ማሳደግ እና የግብርና ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ እንዳለባት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ምሁራን ግድቡን ኢትዮጵያ በድል ብታጠናቅቅም ተጠቃሚነቷን ይበልጥ ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ በፍትሐዊነት ውኃን እያሠራጨች መኾኑን ለዓለም ማሳወቅ ከምሁራን እንደሚጠበቅም ጠቅሰዋል።
ግብጽ ለራሷ ተጠቃሚነት ስትል በጋራ መሥራትን አማራጭ እንድታደርግ የዲፕሎማሲ ዘርፉን ይበልጥ መጠቀም እንደሚገባም ጠቁመዋል። የሕዳሴ ግድቡ ለግብጽ የተዘጋ ምዕራፍ መኾኑንም ጠቁመዋል።
👉 ሌላኛው የግብጽ ሴራ
የሕዳሴ ግድብ እንዳይሳካ ያደረገችው ሴራ ያልተሳካላት ግብጽ ኢትዮጵያ በውስጥ ችግሮች እንድትፈተን ታጣቂዎችን በመመልመል እና በመደገፍ ግጭትን ለማስፋት እየጣረች ነው።
ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት በመፍታት፤ ሰላምን በማጽናት፤ የልማት ሥራዎችን ውጤታማ በማድረግ፤ አንድነትን በማረጋገጥ የግብጽን ሴራ ማክሸፍ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚጠበቅ ተግባር ነው።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን የነገ ዕድል የሚወስን የጋራ መላ ነው።
Next articleየ8ኛ ክፍሉ ተማሪ ለአርሶ አደሮች ተስፋ የኾነ ፈጠራ ይዞ መጥቷል