በቡሬ ከተማ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ የኾነው ፍጹም አማረ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በየዕለቱ የሚገጥማቸውን የድካም፣ የጊዜ እና የሰብል ውድመት ችግር በቅርበት የታዘበ የድንቅ አዕምሮ ባለቤት ነው። እናም እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ለችግሩ ዘመናዊ እና ድንቅ መፍትሔ ይዞ ብቅ ብሏል።
ተማሪ ፍጹም “ኢኮ ስፕሬይ ኤክስ” የተሰኘች የግብርና ድሮን ቴክኖሎጂን በመፍጠር ብቅ ብሏል። ይህች ድንቅ የፈጠራ ሥራ በግብርናው ዘርፍ ትልቅ ብሥራት ይዛ የመጣች ናት። በአንድ ጊዜ አራት ዓበይት ተግባራትን የማከናወን ብቃት አላት ነው ያለው ታዳጊው ተማሪ ፍጹም።


ድሮኗ ፀረተባይ ኬሚካል መርጨት አንዱ ተግባሯ መኾኑን ተናግሯል። አርሶአደሮች ኬሚካል በጀርባቸው ተሸክመው ያለምንም የጤና ጥንቃቄ ሲረጩ የሚደርስባቸውን የጤና እና የጊዜ ጉዳት ፈጽሞ ማስቀረት እንደምታስችል ነው የገለጸው።


ፈሳሽ ማዳበሪያ ማሰራጨት ደግሞ ሌላኛው ተግባሯ እንደኾነ ጠቁሟል።


አርሶአደሮች በጠጣር ማዳበሪያ በኮርኪ እና መሰል ቁሳቁስ ማዳበሪያ ለመጨመር የሚያደርጉትን ድካም እና ጊዜ በማስቀረት በደቂቃዎች ውስጥ ሙሉ ማሳውን እንደሚያደርስ ነው የተናገረው።


ሌላኛው ተግባሯ ሰብል አጥፊ አንበጣዎችን ማባረር ነው ብሏል። ለአካባቢው አደጋ የኾኑትን የፀረሰብል ነፍሳት እና የአንበጣ መንጋዎችን በብቃት ታባርራለች።


የመስኖ ውኃም ታጠጣለች። በባሕላዊ መስኖ የአፈር መሸርሸር እንዳይከሰት እና በማደግ ላይ ያሉ ቡቃያዎች ሥር ለፀሐይ ተጋልጠው እንዳይደርቁ መጠንቀቅ የሚያስችል የውኃ እርጭት ታከናውናለች ብሏል።

ፍጹም ይህንን ድሮን ለመሥራት የተለያዩ ሞተሮች፣ ፓምፕ፣ ኖዝሎች፣ የአልሙኒየም ፍሬሞችን እና ሌሎችንም ግብዓቶች በፈጠራ ብቃቱ አስተካክሎ እንደተጠቀመ ከአሚኮ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።
የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ኾኖ እንደዚህ ያለ አርቆ አስተዋይነት እና ሀገር በቀል መፍትሔ ይዞ መምጣት ለሀገር ትልቅ ተስፋን የሚያሳይ ነው።

ለዚህ ደግሞ እንዲህ ዓይነት የፈጠራ ባለቤቶችን በማበረታታት እና በመደገፍ ራሳቸውን እና ሀገርን እንዲጠቅሙ ማድረግ ይጠበቃል።

እባክዎ ለዚህ ታዳጊ እና ለፈጠራው ያለዎትን አድናቆት እና አበረታች አስተያየት በሃሳብ መስጫው ላይ ያስቀምጡለት?


ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ