
ዓባይ ባንክ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ለሚገኘው ዝግባ የሕጻናት እና አርጋውያን በጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ አድርጓል።
የዓባይ ባንክ ባሕርዳር ዲሥትሪክት ምክትል ዋና መኮንን አልማው ወርቅነህ ዓባይ ባንክ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ የኅብረተሰቡን ክፍተቶች ለመሙላት በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ባንኩ የአዲስ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ 700ሺህ ብር የሚገመት ለዝግባ ሕጻናት እና አረጋውያን በጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት።
ባንኩ በክልሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን የመደገፍ ሥራ መሥራቱን አንስተዋል። ከመደበኛ አገልግሎት ባለፈ እንዲህ አይነት ድጋፎች የባንኩ ትኩረቶች ናቸው ብለዋል።
ባንኩ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ማኅበራዊ ችግሮችን ትኩረት አድርጎ መፍትሔ ለመስጠት እየተጋ የሚገኝ ነው ብለዋል። በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ድጋፉን የተረከቡት የዝግባ ሕጻናት እና አረጋውያን በጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አሥኪያጅ ሥለሺ ጌታቸው ድርጅቱ ከ4ሺህ በላይ ደጋፊ የሌላቸውን ሕፃናት እና አረጋውያንን በመደገፍ ላይ የሚገኝ ነው ብለዋል። በዓልን ምክንያት በማድረግ ዓባይ ባንክ 300ሺህ ብር የሚጠጋ የምግብ ዘይት ድጋፍ እና 400ሺህ የካሽ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት።
ይህ ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት እና የልጆችን የዕለት ተዕለት የምግብ ፍጆታ ፍላጎት ለማሳካት እንደሚውልም ተናግረዋል። ድጋፉ ለድርጅቱ የቤት ግንባታ የሚያገለግል እንደኾነም ጠቁመዋል። ለሕጻናቱ እና ለአረጋውያኑ ፈገግታ ምክንያት ለኾነው ዓባይ ባንክም ምሥጋና አቅርበዋል።
የተደረገው ይህ አርዓያነት ያለውን ተግባር ሌሎችም ተቋማት ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
