‎”ነገ ሀገራችን ምን ትኾናለች?” የሚለውን ታሳቢ ያደረገ አቅጣጫ መያዝ ይገባል።

10
‎”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025″ ስትራቴጂ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች መሠረት በማድረግ የተነደፈው “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ፣ ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ ታጅባ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ የሚያስችል የትውልድ ርዕይ ማዕቀፍ ነው።
‎ይህ ስትራቴጂ የዲጂታል አገልግሎቶችን ተደራሽነት ከማስፋት ባለፈ የተቋማትን አሠራር በማዘመን ዜጎች በዓለም አቀፍ የዲጂታል መስመር ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ለማስቻል ትልልቅ ዓላማዎችን አንግቦ እየተተገበረ ይገኛል።
‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የ«ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030» ስትራቴጂ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ እንደገለጹት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው «ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025» ስትራቴጂ ስኬታማ ኾኖ መጠናቀቁን አውስተዋል።
‎አዲሱ የ«ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030» ስትራቴጂ ሦሥት ቁልፍ ዓላማዎች እንዳሉት የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመጀመሪያው ሁሉም ዜጎች ባሉበት ቦታ ኾነው የሚፈልጉትን አገልግሎት የሚያገኙበትን ዕድል መፍጠር እንደኾነ ገልጸዋል።
‎ሁለተኛው ዜጎችን እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ ሲኾን፣ ሦሥተኛው ደግሞ በዜጎች እና በተቋማት መካከል ጠንካራ መተማመንን መገንባት እንደኾነ አስረድተዋል።
‎በሂደቱም በመንግሥት እና በግል ተቋማት መካከል የተቀናጀ ግንኙነት የመፍጠር፣ አስተማማኝ የሳይበር ጥቃት መከላከል ሥርዓት የመዘርጋት እና ቴክኖሎጂ-ሳቢ ትውልድ የመገንባት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
‎አክለውም የሳይበር ደኅንነትን ማረጋገጥ እና የዜጎችን የዲጂታል አጠቃቀም ማሳደግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያሰመሩበት ሲኾን በቴክኖሎጂ የበለፀገ ትውልድ ሲፈጠር የሀገርን ባሕል፣ ፍላጎት እና ጥቅም ባልነካ መልኩ መኾን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
‎የዲጂታል ሉዓላዊነት የዘመኑ ወሳኝ ጉዳይ በመኾኑ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ራሷን መቻል እንዳለባት እና ለዚህም የዘርፉን ተቋማት አቅም የማጎልበት ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
‎የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) የሰው ልጅ ዕውቀት እና የአኗኗር ዘይቤ በከፍተኛ ፍጥነት እየተለወጠ መምጣቱን በማንሳት በዲጂታል የጎለበተ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
‎ባለፉት ዓመታት የተቀረጹ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች አጠቃላይ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመገንባት ሰፊ መሠረት መጣላቸውን ያመለከቱት ሚኒስትሩ ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት «ነገ ሀገራችን ምን ትኾናለች?» የሚለውን ታሳቢ ያደረገ አቅጣጫ መያዙን ገልጸዋል።
‎ባለፉት ዓመታት የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ቀልጣፋ አሠራር መዘርጋቱን የጠቆሙት ሚኒስትሩ በቀጣይም የነገ ልጆች የሚረከቧትን ሀገር በቴክኖሎጂ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ አሳስበዋል።
‎ለዚህም ተቋማቸው ከሃሳብ ማመንጨት ጀምሮ እስከ ግዙፍ የዲጂታል ማዕቀፎች ዝግጅት ድረስ በትጋት እየሠራ ይገኛል።
‎በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) እና በኮዲንግ ኢኒሼቲቮች የታገዙ የዲጂታል ክህሎት እና የፈጠራ ሥራዎችም ወጣቶችን ለነገው ዓለም ዝግጁ ለማድረግ ታቅደዋል።
‎በአጠቃላይ «ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030» ከቀላል የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባሻገር በፈጠራ እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ እውን የሚያደርግ ታላቅ ሀገራዊ ምዕራፍ ነው።
‎በሥራውድንቅ ደሳለው
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleእንኳን ለ2019 አዲስ ዓመት አደረሳችሁ
Next articleለሕጻናቱ እና ለአረጋውያኑ ደስታ እየተሠራ ነው።