
ኢትዮጵያ በታሪኳ ረጅም የሀገር መንግሥት ግንባታ ሂደት ያሳለፈች ቢኾንም ሂደቱ ሙሉ በሙሉ በሕዝቦች መካከል ባለው አጠቃላይ ስምምነት ላይ የተመሠረተ ባለመኾኑ አሥተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ለዘመናት ሲንከባለሉ ቆይተዋል።
የሕገ መንግሥት አሳታፊነት፣ በክልሎች እና በብሔረሰቦች የሚነሱ የማንነት እና የወሰን ውዝግቦች፣ እንዲሁም የእኩልነት እና የአካታችነት ጥያቄዎች በየጊዜው ለሚከሰቱ ግጭቶች፣ ለፖለቲካ አለመረጋጋት እና ለዜጎች መፈናቀል ዋነኛ መንስኤ ኾነዋል።
ታዲያ እነዚህን ሥር የሰደዱ ቁስሎች በዘላቂነት ለማከም መንግሥት በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 መሠረት አካታች፣ አሳታፊ እና ገለልተኛ የኾነውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
በአሁኑ ወቅትም ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ማኅበራት በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ብሔራዊ መግባባት እና ጠንካራ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት የተጣለበት ኀላፊነት ከፍተኛ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በቅርቡ ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካውያን ወሳኝ መድረክ መኾኑን አንስተዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ የቅርብ ጊዜ ችግሮችን ለመፍታት ብቻ ሳይኾን ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በጋራ ለመመለስ ያለመ መኾኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም መድረኩ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ ሃሳቦችን የሚያስቀጥል፣ ውስንነቶችን ደግሞ የአንድነትን ገመድ በሚያጠናክር መልኩ የሚያርም እና የሚያሻሽል መኾኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ፖለቲካዊ እና አሥተዳደራዊ ስብራቶችን ለመጠገን የሚያስችል ትልቁ እና ታሪካዊው መድረክ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
በምክክር ሂደቱ ተቃራኒ ዕይታ ያላቸው ወገኖች በግልጽ፣ በነፃነት እና በሠለጠነ መንገድ የሚወያዩበት ጭምር መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘላቂ ሰላም፣ ብሔራዊ መግባባት እና ጠንካራ ሀገር መገንባት የሚቻለው በሕዝቦች መካከል ዕውነተኛ ውይይት ሲኖር ብቻ ነው። በመኾኑም እያንዳንዱ ዜጋ ከጥል እና ከልዩነት ይልቅ ንግግርን፣ ከጠብ ይልቅ ዕርቅን በማስቀደም የዚህ ታሪካዊ ሂደት አካል እና ባለቤት ሊኾን እንደሚገባም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
