የጣናዋ እመቤት ባሕር ዳር ከተማ አዲስ ገጸ በረከት!

9
✈️ የውበት ሰገነቷ ባሕር ዳር ከተማ ዛሬም ካባዋን ደርባ በዓለም አደባባይ ትደምቅ ዘንድ የደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሌላኛው ግርማዋ ኾኗል። ከተፈጥሮ ውበቷ እና ከታሪክ ሃብቷ ጋር ጸጋ ተደራርቦ የተሰጣት ከተማዋ በኮሪደር ልማት አምራ፣ ደምቃ፣ ተሞሽራ እና ጣናን ተንተርሳ ኑ ይጎብኙን እያለች ትገኛለች።
የደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማራኪ ውበቷን ጨምሮ ዝናዋን የሚያጎላ ሌላኛው ታላቅ ምዕራፍ ነው ማለት ይቻላል። በዚህም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷ እጅግ ከፍ ይላል። ባሕር ዳር ከተማ ስትታሰብ የጣና ሐይቅ፣ የባሕር ዳር ዓሣ እና ሌሎችም በረከቶች በውስጧ አብረው ይነሳሉ።
ሰማይ እና ምድር የተስማሙበት ማራኪ ድባቧ እና ከጣና የሚመጣው ለስላሳ የአየር ጸባይ የከተማዋ ለየት ያለ መልክ እና ጸጋ ነው። ይህም ከቱሪዝም የሚገኘውን ኢኮኖሚ በእጅጉ እያነቃቃ እና እያሳደገ ይገኛል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው ከተማዋ የቱሪዝም መዳረሻነቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየጎላ የመጣችው ውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ የሚያቀላጥፍ እና ዓለም አቀፍ ተደራሽነቷን የሚያሰፋ ታላቅ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ከሰሞኑ የተመረቀው ዘመናዊው የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለከተማዋ የቱሪዝም ፍሰት እና የኢኮኖሚ ማዕከልነት ሌላ ገጽታ የፈጠረ ቁልፍ መሠረተ ልማት መኾኑንም ተናግረዋል።
የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ባሕር ዳር መምጣት ለሚፈልጉ ቱሪስቶች ከፍተኛ ምቾት ፈጥሯል ነው ያሉት። አውሮፕላን ማረፊያው ጎብኝዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደሚፈልጉት መዳረሻ እንዲደርሱ ከማድረጉም በላይ ራሱ የቱሪዝም መዳረሻ አካል በመኾን የከተማዋን ተፈላጊነት ከፍ አድርጎታል ነው ያሉት።
ይህ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ጎብኝዎች ባሕር ዳርን እንዲመርጡ ዋነኛ መሠረት ኾኖ እንደሚያገለግል እና የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ የሚቀይር መኾኑን ነው የተናገሩት።
​ባሕር ዳር ከተማ በርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም ሀብቶች ያሏት ከተማ እንደኾነችም ገልጸዋል። የጣና ሐይቅ ገዳማት፤ ደሴቶች፣ የኮሪደር ልማት እና የተለያዩ መዝናኛ ሥፍራዎች ተፈጥሯዊ ውበታቸውን ጠብቀው የሚገኙ እና የብዙዎችን ቀልብ የሚስቡ ስፍራዎች ናቸው ብለዋል።
በከተማዋ የሚገኙ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ የውኃ፣ የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት አማራጮች ለቱሪስቶች የጉዞ ቆይታ ልዩ ውበት ሰጥተዋቸዋል ነው ያሉት። በዘርፉ ወጣቶች ተደራጅተው በራይዶች፣ በኤርፖርት ታክሲዎች እና በአስጎብኝዎች በማንኛውም ሰዓት ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገር ጎብኝዎች ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በከተማዋ የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶች እና ሌሎችም ለዕይታ ማራኪ ገጽታዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል። ይህም ጎብኝዎች በከተማው ውስጥ የሚቆዩበትን ጊዜ እንዲያራዝሙ ትልቅ ዕድል ይሠጣል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያው የቱሪዝም ዘርፉን በመነቃቃት ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር እንደኾነም አንስተዋል።
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበፋርጣ ወረዳ የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን ሰብል በበጎ ፈቃድ የማረም እና የመንከባከብ ሥራ እየተከናወነ ነው።
Next articleሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን የነገ ዕድል የሚወስን የጋራ መላ ነው።