በፋርጣ ወረዳ የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን ሰብል በበጎ ፈቃድ የማረም እና የመንከባከብ ሥራ እየተከናወነ ነው።

9

በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን ሰብል የማረም እና የመንከባከብ ሥራ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል።

በወዋ ማገራ ቀበሌ በተካሄደው በዚህ መርሐ ግብር በጎ ፈቃደኞች ድጋፍ በሚሹ አርሶ አደሮች ማሳዎች ላይ ተሰማርተው የበጎ ፈቃድ ሥራውን ሠርተዋል።

ሰብላቸው የታረመላቸው አርሶ አደር መንግሥቱ መርሻ እንደገለጹት የተደረገላቸው ድጋፍ ጊዜ እና ጉልበታቸውን ከመቆጠቡ ባሻገር ሰብላቸው በወቅቱ ታርሞ የተሻለ ምርት እንዲያገኙ የሚያስችል በመኾኑ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

የፋርጣ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ይርጋ ጌትነት በወረዳው በችግኝ ተከላ፣ በደም ልገሳ እና በቤት እድሳት ሲከናወኑ የቆዩ የሕዝባዊ አገልግሎት ሥራዎች አሁንም ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

አሥተዳደሩ ድጋፍ የሚሹ አርሶ አደሮችን በመለየት የአረም ሥራውን ከመደገፍ ባለፈ በግብርና ባለሙያ ክትትል እንዲደረግላቸው እንደሚሠራም አክለው ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የፋርጣ ወረዳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አማረ ይሁኔ በበኩላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የማኅበረሰብ እሴት እና መስተጋብርን የሚያጎለብት መኾኑን ጠቁመዋል።

አክለውም ድጋፉ በአረም ሥራ ብቻ እንደማይወሰን እና ሰብሉ ታጭዶ እና ተወቅቶ እስከሚሠበሠብ ድረስ እገዛው እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በበጎ ፈቃድ ሥራው የተሳተፉ ዜጎችም እንዲህ ያሉ ሰብዓዊ ተግባራትን በባለቤትነት ማከናወናቸው ከፍተኛ የሕሊና እርካታ እንዳጎናጸፋቸው ገልጸዋል።

#AMECO #FartaWoreda #SouthGondar #Ethiopia

#ደብረ_ታቦር #ነሐሴ_04_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ተክለብርሃን ፈንታ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበደብረ ማርቆስ ከተማ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ እየተሠራ ነው