
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በሚገኙ የተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያጋጠሟቸውን የመሠረተ ልማት እና የመብራት ችግሮች በመለየት የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ያለመ የሥራ ምልከታ አድርገዋል።
በምልከታው ወቅትም ፋብሪካዎች የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ከመድፈድረግ ባለፈ ምርቶቻቸውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች እና የውጭ ሀገራት ለመላክ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ፋብሪካዎች አቅማቸውን አውጥተው ለማምረት ግን የመብራት እና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ሊሟላላቸው እንደሚገባ ነው የተመላከተው።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ተመስገን ተድላ በአካባቢው በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም ምክንያት የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ብቻ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 25 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማውጣታቸውን እና ያጋጠሙ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል።
የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ እንደተናገሩት በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት በግብርና፣ በማዕድን እና በተለያዩ ዘርፎች ከ522 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል።
አክለውም በበጀት ዓመቱ 174 መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በአዲስ መልክ ሥራ በመጀመራቸው ለ100 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማም የሚታዩ የመብራት እና መሰል የመሠረተ ልማት ማነቆዎችን በመፍታት የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ ቢሮው በትኩረት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
#Ameco #DebreMarkos #AmharaInvestment #EthiopianIndustry
#ደብረ_ማርቆስ #ነሐሴ_04_2018_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
