
በእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በማኅበር ተደራጅተው የቤት መሥሪያ ቦታ ሲጠባበቁ ለቆዩ 115 ማኅበራት መሬት ለማስረከብ የሚያስችል የብሎክ ዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በዕጣ አወጣጡ ላይ 115 ማኅበራት ናቸው የተሳተፉት። ይህም 2 ሺህ 719 ዜጎችን የቤት መሥሪያ ቦታ ፍላጎት ይመልሳል ነው የተባለው።
በዕጣ አወጣጡ ላይ የተገኙት የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ የብሎክ ዕጣ ላወጡ ማኅበራት ከሦሥተኛ ወገን የፀዳ 148 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ዕጣ ላወጡ ማኅበራት በፍጥነት መሬት ለማስረከብ የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።
አሁንም በማኅበር ተደራጅተው መሬት የሚጠባበቁ በርካታ ማኅበራት መኖራቸውን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በሂደት የሁሉንም ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
በሁነቱ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ መንግሥት በመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና አቅርቦት መካከል የሚስተዋለውን አለመጣጣም ለመፍታት የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን ዘርግቶ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በማኅበር ለተደራጁ ማኅበራት የመሬት አቅርቦትም አንዱ አማራጭ ነው ብለዋል።
ልማት የሰላም ውጤት ነው ያሉት ኀላፊው በቀጣይ ሰላምን እያፀኑ የዜጎችን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።
በመድረኩ በሕግ ማስከበር ወቅት ለተሰው 18 የሰላም አስከባሪ አባላት ቤተሰቦችም ከተማ አሥተዳደሩ የመሬት ካሳ በመሸፈን የብሎክ ርክክብ አካሂዷል።
#AMECO #AwiZone #አማራክልል
#እንጅባራ #ነሐሴ_04_2018_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
