
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ከፌዴራል የመንግሥት ግዥ እና ንብረት ባለሥልጣን ጋር በመቀናጀት የኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዥ ሥርዓትን በክልሉ ለመተግበር ለተመረጡ አስር ተቋማት የግዥ ባለሙያዎች እና የሥራ ኀላፊዎች ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ አታላይ ጥላሁን እንደገለጹት አሠራርን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የማዘመን እና የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
የሕዝብ ሃብትን በቁጠባ እና በተቀላጠፈ መልኩ ለማሥተዳደር የሚያስችለውን አዲሱን አሠራር በ2019 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍ፣ የመመሪያ እና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።
አክለውም የአስሩ ተቋማት የሙከራ ትግበራ ስኬታማነት ሥርዓቱን እስከ ታችኛው የመንግሥት እርከን ለማስፋት መሠረት እንደሚኾንም ጠቁመዋል።
በፌዴራል የመንግሥት ግዥ እና ንብረት ባለሥልጣን የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ፕሮጀክት የአቅም ግንባታ አሥተባባሪ ደበበ ማሞ በበኩላቸው ሥርዓቱ በ2014 ዓ.ም በዘጠኝ የፌዴራል ተቋማት ተጀምሮ በ2017 ዓ.ም በሁሉም የፌዴራል ተቋማት ቅርንጫፎች እና ዩኒቨርሲቲዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።
አሠራሩ ከወረቀት እና ከሰው ንኪኪ ነፃ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ በመኾኑ ወጥ የኾነ ሀገራዊ ሥርዓት ለመዘርጋት ወደ ክልሎች የማውረድ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በሥልጠናው እየተሳተፉ የሚገኙ የግዥ ባለሙያዎች እስካሁን የነበረው ወረቀትን መሠረት ያደረገ አሠራር የተንዛዛ እና አሰልች እንደነበር ገልጸው የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓቱ መተግበሩ ጊዜን፣ ጉልበትን እና ወጭን ከመቆጠቡ ባሻገር ሙስናን በመከላከል እና እንግልትን በማስቀረት አገልግሎቱን በከፍተኛ ሁኔታ ያቀላጥፋል ሲሉ ተናግረዋል።
#Ameco #eGP #DigitalProcurement #PPPA
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_04_2018_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
