
የበሬ አንገት እርሻ ታሪክን ለመለወጥ የሰነቀው ባለራዕይ ታዳጊ ከፍኖተሰላም 🚜🌾
ኢትዮጵያ ውስጥ በበሬ ትክሻ እና በአርሶአደሮች ድካም ላይ የተመሠረተው የእርሻ ሥራ ዘመናትን አስቆጥሯል። አብዛኛው አርሶአደር ከድካሙ ሳይላቀቅ ጊዜውን እና ጉልበቱን እየገበረ በዚያው በጥንታዊ መንገድ የእርሻ ሥራውን እየከወነ ቆይቷል። ይህንን የታሪክ እና የዕድገት ቅኝት ለመቀየር ግን አንድ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ብቅ ብሏል። ታዳጊው ተማሪ ደረጀ ተሾመ።
ከፍኖተ ሰላም ከተማ የወጣው ይህ ታዳጊ ባለራዕይ የአፈርን እና የሰብልን ሁኔታ ያገናዘበ፣ የአርሶ አደሮችን እና የበሬውን ድካም የሚያቀል ትንሽ ትራክተር ነው በጥበብ ያስተዋወቀው።
💡 የተማሪ ደረጃ ፈጠራ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?
የጉልበት እና የጊዜ ቁጠባ አንዱ ነው። በበሬ ሲታረስ አራት ቀን የሚወስደውን የአንድ ሄክታር መሬት እርሻ ይህች ትንሽ ትራክተር በአንድ ቀን ብቻ አጠናቅቃ ታስረክባለች። የወሰን አጥር የሌለው እርሻ ትከውናለች። ትልልቅ ትራክተሮች ኩታገጠም ባልኾኑ እና ጠበብ ባሉ አነስተኛ ማሳዎች ላይ ለማረስ የሚቸገሩትን የተማሪ ደረጃ ፈጠራ ወሰን እየጠበቀች እያንዳንዱን ማሳ በጥራት ታርሳለች።
ባለ ብዙ አገልግሎት መኾኗም ልዩ ያደርጋታል። በጥቅም ላይ የማይውሉ (የተበላሹ) የሞተር ሳይክል ጊር ቦክሶችን በመጠቀም የተሠራችው ይህች ማሽን እርሻ ማረስ ብቻ ሳይኾን የውኃ ፓምፕ ተገጥሞላት ማሳን የመስኖ ውኃ ማጠጣትም ትችላለች። ከፍተኛ የመሳብ አቅም ያላት መኾኑም ልዩ ያደርጋታል።
💰ዋጋዋ ትራክተር መጠቀም ፈልጎ የገንዘብ ውስንነት ለገጠመው አርሶአደር የምትታደግ መኾኗን የፈጠራ ባለቤቱ ተናግሯል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ የትራክተር ዋጋ እስከ 4 ሚሊዮን ብር ዋጋ ይጠጋል ያለው የፈጠራ ባለቤቱ ይቺ ትንሽ ትራክተር የወጣላት አሁናዊ ዋጋ ግን ገበያ ላይ ካለው 1ነጥብ 5 በመቶ በታች እንደኾነ ጠቅሷል።
የኢኮኖሚ ፈተናውን ያጠናው ተማሪ ደረጃ ማሽኑን አርሶአደሮች የአንድ በሬ ዋጋ ሊባል በሚችል ማለትም በ70 ሺህ ብር ብቻ ገዝተው እንዲጠቀሙበት አድርጎ አቅርቦታል። በ1ሊትር ነዳጅ ብቻ እስከ 4 ሰዓት በማረስ የአርሶ አደሮችን ወጭ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳልም ብሏል።
🚀ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረገው የፈጠራ ባለቤቱ የተማሪ ደረጃ ፈጠራውን ከንድፈሀሳብ ወደ ተግባር ለመቀየር ማኅበረሰቡ አዲሱን ቴክኖሎጂ አይቀበለውም የሚል ስጋት የነበረው መኾኑን ገልጾ በአካባቢው የታየው አቀባበል እና ፍላጎት ግን እጅግ የሚያስደስት መኾኑን ተናግሯል።
ፈጠራውን በመፍጠር ብቻ ሳይወሰን የራሱን ድርጅት ፈቃድ አውጥቶ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማሟላት በ3 ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀችውን ትራክተር ለገበያ ለማቅረብ በሥራ ላይ ይገኛል።
🤝 ፈጠራውን ወደ ተግባር እየቀየረ ያለው ወጣት አርሶአደሮችን በብዛት የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እያደረገ ላለው እንቅስቃሴ የባለሀብቶች እና የተቋማት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።
ይህ የፈጠራ ሥራ ከግል ጥረት አልፎ የሀገር ሀብት እንዲኾን ባለሀብቶች እና ኢንቨስተሮች የፋይናንስ እና የምርት አቅም በመፍጠር፣ የመንግሥት እና የግል ተቋማት በሚያዘጋጇቸው ኤክስፖዎች ላይ ቦታ በመስጠት እና ዩኒቨርሲቲዎች እና የስቲም ሴንተር ማዕከላት ቴክኖሎጂውን ወደ ሰፊ ፋብሪካ በማሸጋገር እንዲያግዙም ጥሪ አቅርቧል።
#EthiopianInnovators #STEMEthiopia #FinoteSelam🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_04_2018_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ፦ በሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
