በሃሳብ ምንጮች ታጅቦ ለጠንካራ ሀገራዊ አንድነት የሚደረግ ጉዞ

18

🇪🇹በሃሳብ ምንጮች ታጅቦ ለጠንካራ ሀገራዊ አንድነት የሚደረግ ጉዞ

​ኢትዮጵያ የበርካታ ዘመናት የሀገረ መንግሥት ታሪክ፣ ባለጸጋ ባሕሎች እና የተለያዩ ሃይማኖቶች ባለቤት እንደ መኾኗ መጠን፤ ከሺህ ዘመናት በላይ በአብሮነት እና በመከባበር የዘለቀች ሀገር ናት። ዛሬም በታሪካዊ እና ፖለቲካዊ የጊዜ ሂደት የተፈጠሩ ልዩነቶችን በንግግር እና በመደማመጥ ለመፍታት ታሪካዊ የኾነ ሀገራዊ ምክክር እያካሄደች ትገኛለች።

​በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ምስክር ከተማ ሀገራዊ ምክክር ልክ እንደ ቤተሰብ በጋራ ችግሮቻቸው ላይ ተመካክረው እንደሚፈቱት ሁሉ በሕዝቦች መካከል ያሉ የዘመናት አለመግባባቶች የሚፈቱበት ትልቅ የሰላም መድረክ ነው ይላሉ።

​መምህሩ የሐሳብ ልዩነት እንደ ዕድል መታየት እንዳለበትም አንስተዋል። በምክክር ሂደቱ ውስጥ የሚነሱ የሃሳብ መለያየቶች እና ፍጭቶች እንደ መጥፎ አጋጣሚ ሊወሰዱ እንደማይገባ የገለጹት መምህሩ ይልቁንም የሃሳብ ፍጭት ውይይቱ በስሎ የጠራ ሃሳብ እንዲመጣ እና የጋራ መግባባት እንዲፈጠር ትልቅ ዕድል ይሰጣል ብለዋል።

“ፍጭት እና ክርክር ከሌለ ምክክር ራሱ አያስፈልግም ነበር” የሚሉት መምህሩ፣ የምክክሩ ዋና ዓላማም በሃሳብ ፍጭት ውስጥ አልፎ የጋራ ሃሳብ ማራመድ መኾኑን አስረድተዋል። በዚህም መከባበር እና መደማመጥ ይነግሳል ብለዋል።

በሃሳብ መለያየት ማለት አለመስማማት ማለት አይደለም፤ ይልቁንም በመቀባበል እና በማስተዋል ወደ የተሻለ ሃሳብ የመሸጋገሪያ መንገድ ነው እንጂ ብለዋል። ምክክር የውድድር መድረክ ሳይኾን የጋራ መግባቢያ በመኾኑ አሸናፊ እና ተሸናፊ ሳይኖር የሃሳብ የበላይነት ብቻ መረጋገጥ እንዳለበት ነው የገለጹት።

​ኢትዮጵያውያንን ከሚያራርቁት ይልቅ የሚያቀራርቡ እና የሚያስተሳስሩ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ነው መምህሩ ያስረዱት።

እንደ መምህሩ ገለጻ የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ብዙ ጠላቶች ሚነዙትን ሀሰተኛ መረጃ ማገናዘብ ያስፈልጋል። ተመካክሮ ሀገር መገንባት እንጂ መደናገር አያስፈልግም ነው ያሉት። ኅብረተሰቡ መረጃዎችን ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መግለጫዎች እና ከታማኝ የሚዲያ ተቋማት ብቻ መከታተል ይገባዋልም ብለዋል።

​ኢትዮጵያ በቀላሉ የማትፈርስ እና የረጅም ዘመን የአብሮነት እሴት ያላት ሀገር እንደኾነችም ጠቅሰዋል። በምክክር ሂደት በመግባባት ለጋራ ሀገር በጽናት መቆም የሁሉንም ዜጋ ድርሻ እንደሚጠይቅም ነው የገለጹት። ሀገራዊ ምክክር ጊዜን እና ትዕግስትን ይጠይቃል ብለዋል። የኢትዮጵያን አንድነት እና ሰላም አስተማማኝ ማድረግ ታሪካዊ ፋይዳው የጎላ በመኾኑ ለስኬታማነቱ በጋራ መሥራት እንደሚገባም ተገልጿል። በዚህም የነገ ትውልድን እና መጻኢ ሀገርን ማሰብ እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል።

#Ethiopia#NationalDialogue #Peace🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_04_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት የት ደረሰ?
Next articleየበሬ አንገት እርሻ ታሪክን ለመለወጥ የሰነቀው ባለራዕይ ታዳጊ ከፍኖተሰላም