የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት የት ደረሰ?

13

📌 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት የት ደረሰ?

የኮሚሽኑ አሁናዊ መረጃ፦

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት እየተጠናከረ እና ወደ ተሻለ ደረጃ እየተሸጋገረ መኾኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ ስለ ሂደቱ አሁናዊ ሁኔታ እና በምክክሩ ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች የሰጡት ማብራሪያ ዋና ዋና ነጥቦች፦

👉የምክክር ሂደቱ እና የ500ዎቹ ቡድን ሥራ፦

ከዚህ ቀደም በሁለት የ250 ቡድኖች የተነሱ ሀሳቦችን ለማጠናቀር ከእያንዳንዱ 15 አባላት የተወጣጡ 30 አጠናቃሪዎች ሃሳቦችን ሰንደው 500 አባላት ላሉት ቡድኖች ማቅረብ ጀምረዋል ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም 3 እና 4 የሚኾኑ የአጀንዳ ቡድኖች በ500 አባላት ደረጃ ምክክራቸውን የጀመሩ መኾኑን እና ቀሪዎቹ እስከነገ ድረስ ሂደቱን እንደሚቀላቀሉ ገልጸዋል።

👉ስለ አለመግባባቶች እና ጭቅጭቆች የተሰጠ ማብራሪያ፦

በምክክሩ የመጀመሪያ ምዕራፎች ላይ አለመግባባቶች፣ ክርክሮች እና ስሜታዊነት መንጸባረቃቸው ተፈጥሯዊ እና በውይይት ሂደት ውስጥ የሚጠበቅ እንደኾነም ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። ሂደቱ ከታች ከ10 ተመካካሪዎች ጀምሮ እያደገ የመጣ ሲኾን አሁን ላይ የግል እና የቡድን ሃሳቦችን በመተው ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረጉ የጋራ ሃሳቦች ወደ መሀል እየመጡ ይገኛሉ ብለዋል።

👉ውሳኔ ወይስ የምክር ሀሳብ?

እስካሁን ድረስ በአንድም አጀንዳ ላይ የተሰጠ ውሳኔ የለም፤ ወደፊትም አይኖርም ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ ውሳኔ የሚያሳልፍ ሳይኾን በሕግ አውጭው፣ ሕግ አሥፈጻሚው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሃይማኖት ተቋማት ተባብረው ሀገርን የሚደግፉ የምክር ሃሳቦችን እንዲያዘጋጁ ማገዝ መኾኑን አስገንዝበዋል። በድምጽ ብልጫ ውሳኔ ሊሰጥ ነው ወይም ከውጭ እና ከውስጥ ጫና ተደርጎ ሊወሰን ነው የሚሉ ወሬዎች ሙሉ በሙሉ አሉባልታ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

👉የሥነ-ምግባር ደንብ እና የቅሬታ አፈታት፦

ተሳታፊዎች ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሚኒስትሮች፣ አርሶአደሮች እና አርብቶ አደሮች የተካተቱበት የ120 እና 130 ሚሊዮን ሕዝብ ስሜት ይዘው የመጡ በመኾናቸው ኮሚሽኑ ሂደቱን በትዕግሥት እና በትህትና እየመራ ይገኛል ብለዋል። በምክክሩ ላይ ሀሳብን መደፍጠጥ፣ ማሳፈር ወይም ማንጓጠጥ በሥነምግባር ደንቡ በጥብቅ የተከለከለ እንደኾነም ጠቁመዋል።

የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማስተናገድ ኮሚሽኑ ከፍተኛ ኤክስፐርቶች ያሉበት አሠራር ዘርግቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በመነጋገር መፍትሔ እየሰጠ ይገኛልም ብለዋል።

👉የቀጣይ ጊዜያት ተስፋ፦

የምክክር ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሚገኝ እና በተቀሩት 1እና 2 ሳምንታት ውስጥ ከ4ሺህ ተሳታፊዎች ጋር የሚደረገው የውይይት ምዕራፍ እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል። በመጨረሻም የተሠበሠቡትን 4ሺህ ሃሳቦች አጠናቅሮ ለተግባሪ አካላት በማስረከብ ትግበራቸውን የመከታተል ሥራ እንደሚከናወንም ዋና ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

#NationalDialogue #Ethiopia

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_04_2018_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ፦በሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleሀገርን ከውድቀት መታደጊያ የጥበብ መንገድ
Next articleበሃሳብ ምንጮች ታጅቦ ለጠንካራ ሀገራዊ አንድነት የሚደረግ ጉዞ