የሉዓላዊነት ዋልታ – ጀግንነትን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ያዋሐደ ሠራዊት

6
ኢትዮጵያ ታሪከ ብዙ፣ የነጻነት ማሳያ እና የጀግኖች ሀገር ናት። የዚች ታላቅ ሀገር ሉዓላዊነት እና የድንበር ደኅንነት ተከብሮ ለትውልድ እንዲሻገር ካደረጉት ዋና ዋና አዕማዶች መካከል የሀገር መከላከያ ሠራዊት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በከፍተኛ የሥነ-ልቦና ዝግጅት፣ በጠንካራ ወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት እና በማይናወጥ የሀገር ፍቅር የተገነባ ነው። ለዚህም በታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ ተመስክሮለታል። ሀገር በወረራ በተደፈረች እና ፈተናዎች በተጋረጡባት ወቅት ሁሉ ሕይወቱን ያለ አንዳች ስስት ለሀገሩ በመስጠት ጠላትን አሳፍሮ የመለሰ ባለደማቅ የታሪክ ባለቤትም ነው።
ዛሬም እንደ ትናንቱ ይህ የሀገር ዋልታ ደማቅ ታሪኩን እንዳነገበ ይገኛል። የተረከበውን የአባቶቹን የጀግንነት ታሪክ በማስቀጠል እና የዘመኑን ወታደራዊ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ልህቀት ታጥቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የመከላከያ ሠራዊት ምረቃ ላይ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት ወቅቱ የሚጠይቀውን የውጊያ እና የክትትል ቴክኖሎጂዎችን፤ የሳይበር ደኅንነት እና ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓቶችን መታጠቅ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ስለመኾኑ ማንሳታቸው ይታወሳል። የቴክኖሎጂ ትጥቆችን ከውጭ ከመግዛት ባለፈም በሀገር ውስጥ የማምረት፣ የመጠገን እና የማሻሻል አቅምን መገንባት ለሀገር ደኅንነት መሠረት መኾኑን አንስተው ነበር። ይሁን እና አሁን ላይ ቃል በተግባር ውሏል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በጀግንነት ብቻ ሳይኾን፣ በዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች፣ በዘመናዊ ስትራቴጂካዊ የአየር እና የምድር ኃይል ተገንብቷል። ብቃት ባላቸው መሪዎች ራሱን አጠናክሮ የወቅቱን የዓለም የጦር ሳይንስ ዕድገት በሚመጥን ደረጃ ላይ ደርሷል።
ተቋሙ የውጭ ጥገኝነትን ለመቀነስ እና ራሱን በራሱ ለማጠናከር እያደረገ ባለው ጥረት በሀገር በቀል የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሥራዎች አዳዲስ አቅሞችን እየገነባም ይገኛል።
የወታደራዊ መሣሪያዎችን በራስ አቅም ከማምረት እና ከማደስ ጀምሮ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የፈጠራ ሥራዎችን በተግባር እያዋለ ያለ የሀገር ኩራት ኾኗል። ራሱን በራሱ የማደስ እና የማበልጸግ አቅሙንም በሚያስደንቅ ሁኔታ አሳድጓል።
ተቋሙ የወደፊቷን ዘመናዊት እና ጠንካራ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ታሪካዊ ጀግንነትን ከዘመናዊ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ጋር አዋሕዶ በጽናት እየገሰገሰም ይገኛል።
👉 ክብር ለሀገር መከላከያ ሠራዊት🇪🇹
✍️በሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleአጀንዳ ከመቀበል ወደ መስጠት – የውጭ ጫናን ጥሶ የሚወጣው የኢትዮጵያውያን የጋራ ክንድ
Next articleድንቅ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል የሚንጸባረቅበት_ ጣና ፎረም