ድንቅ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል የሚንጸባረቅበት_ ጣና ፎረም

7
የአማራ ክልል ታላላቅ ሁነቶችን የማዘጋጀት ልምድ አለው። ባለፉት ዓመታት በርካታ ሁነቶችን አዘጋጅቷል። ክልሉ የዳበረ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል አለው። ይህ የዳበረ ባሕል ደግሞ ጎብኘዎች ወደ ክልሉ እንዲመጡ፣ ባሕሉን፣ ታሪኩን እና ሃይማኖቱን እንዲያዩ አድርጓል።
የአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በስኬት ካስተናገዳቸው ሁነቶች መካከል አንደኛው የጣና ፎረም ነው። የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሔ ማግኘት ላይ የሚያተኩረው ይህ ታላቅ መድረክ የትኛውንም መሰናክል ሰብሮ በማለፍ፤ የሰላም፣ የውይይት እና የጋራ መግባባት ችቦ ማብራቱን ቀጥሎበታል።
የጋራ ውይይቶችን በማድረግ በርካታ አዎንታዊ ውጤቶችን ያስመዘገበው የጣና ፎረም ዘንድሮም ለ12ኛ ጊዜ በባሕር ዳር ከተማ በጣና ዳርቻ ይካሄዳል።
ባለፉት ዓመታት ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የሀገር መሪዎች እና የታዋቂ ተቋማት ኀላፊዎች የሚታደሙበት ይህ መድረክ ክልሉ በችግር ውስጥ ኾኖም እንግዶችን በሰላም ተቀብሎ በማስተናገድ ትልቁ የጽናት ማሳያነቱን በተግባር ያረጋገጠበት ነው። ክልሉ የገጠሙትን ሁለንተናዊ ፈተናዎች በመቋቋም ትልልቅ አህጉራዊ እና ሀገራዊ ዝግጅቶችን በውጤታማነት የማስተናገድ ብቃቱን በተደጋጋሚ እያስመሰከረ ይገኛል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ እና በሴኔጋል መካከል የተካሄደውን አህጉራዊ የእግር ኳስ ጨዋታ በስኬት ማስተናገዱ የክልሉን ሁነት የማስተናገድ ጥንካሬ እና አቅም በግልጽ ያሳያል።
በችግር ውስጥ ትጋትን፣ በፈተናዎች ሳይበገር ልማትን፣ ዲፕሎማሲን እና ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ማስቀጠል መቻሉን በተደጋጋሚ እያረጋገጠ ነው። የክልሉ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይነት እና ደግነት ሁነቶች ስኬታማ እንዲኾኑ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
​
ባሕር ዳር ከተማ በኮሪደር ልማቷ ለእንግዶች ምቹነት፣ በጣና ዳርቻ ነፋሻ አየር እና በነዋሪዎቿ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል ከተማዋ የቱሪዝም ማዕከል እየኾነች ትገኛለች። ይህም ቱሪዝሙን ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ በፎረሙ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ፍቅርን፣ሰላምን እና አንድነትን የምንሰጥበት እና ታሪካችንን በተግባር የምናረጋግጥበት ነው ብለዋል።
የማኅበረሰቡን ቱባ ባሕል እና እሴት ለማስተዋወቅ፣ የክልሉን ገጽታ ለመገንባት እና የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማነቃቃት መልካም አጋጣሚ መኾኑም ነው የገለጹት።
ይህንን አጋጣሚ ለመጠቀም ሁሉም የባሕር ዳር እና አካባቢው ማኅበረሰብ ጉባኤውን ስኬታማ ለማድረግ እንደወትሮው ሁሉ የሚጠበቅበትን ኀላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ሥራውድንቅ ደሳለው
Previous articleየሉዓላዊነት ዋልታ – ጀግንነትን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ያዋሐደ ሠራዊት
Next article“ወታደራዊ ቁመናውን የሚያውቁት አይደፍሩትም፤ ይልቁንም ያከብሩታል”