
ስሙ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ አጽናፎች የነገሠ ነው፤ በወጣበት ሁሉ ጀብዱን መጎናጸፍ እና ድል ማድረግ የተፈጥሮ ባሕሪው ነው። እርሱ ለተቸገሩ ወዳጅ ሀገራት ፈጥኖ ደራሽ እና በተሰማራበት ሰማይ ሁሉ የልብ የሚያደርስ ጋሻ ነው። ወታደራዊ ቁመናውን የሚያውቁት አይደፍሩትም፤ ይልቁንም ያከብሩታል፤ ጀግንነቱን ያደንቁታል።
ሁሌም በማይናወጥ ወታደራዊ ግርማ ሞገስ የተሞላ ነው፤ አጋሮቹ ሲያምኑት ጠላቶቹ ደግሞ ይፈሩታል። ሊተነኩሱት የሚያልሙት እንኳ ከሩቅ ከማላዘን ውጭ ወደ እርሱ ለመጠጋት ድፍረቱም ሞራሉም የላቸውም። እርሱ ለቀጣናው ሥጋት ታማኝ ዋስ የኾነው የሰማዩ ዘብ ነው።
ዘመኑ ያፈራቸውን የመጠቁ እና የረቀቁ ቴክኖሎጂዎች ባለቤት ነው፤ በበሰለ ሙያዊ ክህሎት እና በጥበብ የተካነ ነው፤ የማይናወጥ ወታደራዊ ዲሲፕሊንን የተላበሰም ነው።
የደኅንነት ሥጋቶች በዓለማችን ላይ በሚያንዣብቡበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ሀገሩን እና ቀጣናውን በጽናት መከላከል የሚያስችል ዘመናዊ ወታደራዊ አቅም ገንብቷል።
የምሥራቁን እና የምዕራቡን የጂኦ-ፖለቲካ ሽኩቻ ፣ የኀይል ሚዛን አሰላለፍ በጥልቀት የተረዳ ስትራቴጂካዊ ተቋም ነው። ሰማዩን በበላይነት የመቆጣጠር እና የመከላከል አቅሙን ወደ ላቀ ማዕረግ ያሳደገው የአየር ኀይሉ ከውጭም ኾነ ከውስጥ ለሚቃጣ የትኛውም የጠላት ትንኮሳ በሰከንዶች ቅጽበት ምላሽ ለመስጠት ሁልጊዜም በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል።
አየር ኀይሉ የቴክኖሎጂ ልህቀትን ከሰው ኀይል ብቃት ጋር በማቀናጀት የሀገርን ሕልውና የማስከበር ስትራቴጂካዊ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል።
በዚህ የዘመናዊነት ጉዞ ውስጥ አየር ኀይሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖች) የሚያመርትበትን ኢንዱስትሪ ባለቤት መኾን ችሏል። ይህም በኢትዮጵያ የኤሮኖቲክስ ታሪክ ውስጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ያበሰረ አብዮት ነው።
በሀገር ውስጥ የበቁ የኢንጂነሪንግ ጠበብት ባለሙያዎች ዲዛይን ተደርገው የተመረቱት እነዚህ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የጠላትን እንቅስቃሴ ከሰማይ ኾኖ በንቃት ይከታተላሉ፤ መረጃን በጥራት ያጠናቅራሉ።
የትኛውም የደኅንነት እና የጸጥታ ሥጋት ከመከሰቱ በፊት በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን እና ተመጣጣኝ እርምጃ የመውሰድ አቅም አላቸው።
ይህ አቅም ተቋሙ ዘመኑን የዋጀ የጦር መሣሪያ እና የተቀናጀ የመረጃ ሥርዓት ለመታጠቅ ያደረገውን ታላቅ እምርታ የሚያረጋግጥ፣ የረቀቀ ወታደራዊ የቴክኖሎጂ ትጥቁን ወደ ተጨባጭ የውጊያ ድል የሚያሸጋግር የማዕዘን ድንጋይ ነው።
የኢትዮጵያ አየር ኀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አየር ኀይሉ በተግባራዊ ሥልጠና የበሰለ፣ በጽኑ ወታደራዊ ሥነ ምግባር የታነጸ፣ የዘመኑን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ እና በማንኛውም ቅጽበት ለሚሰጥ ሀገራዊ ተልዕኮ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚችል የሰው ኀይል መገንባቱን አረጋግጠዋል።
በውጊያ ወቅት ትክክለኛ እና ፈጣን ምላሽ መስጠት የተቋሙ የሥራ ባሕል መኾኑን ጠቁመዋል። በተለይም ተልዕኮን ያለማወላወል በሰከንዶች ውስጥ መፈጸም የሚችል እና ከፍተኛ ሙያዊ ሥነ ምግባርን የተላበሰ የሰው ኀይል መገንባቱንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኀይል የሀገርን ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ከመጠበቁ ባሻገር ለቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት የማይደፈር የጽናት ማኅተም ኾኖ ቀጥሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
