አሚኮ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን በመወጣት ተተኪ ትውልድ ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።

2
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) መረጃን በልዩ ልዩ አማራጮች ከማሰራጨት ባሻገር በተግባር የተደገፈ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን በመወጣት ተተኪ ትውልድን የመቅረጽ እና የመደገፍ ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል።
የዚሁ በጎ አድራጎት አካል የኾነው የአሚኮ አዲስ አበባ ዘርፍ መሪዎች እና ሠራተኞች በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኘው ወጋገን 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ስጦታ አበርክተዋል።
የኮርፖሬሽኑ የአዲስ አበባ ዘርፍ የንግድ ሥራዎች ዳይሬክተር ታደለ ፋንታሁን እንደገለጹት ተቋሙ ከተለመደው የሚዲያ ሥራው ጎን ለጎን በደም ልገሳ፣ በአረጋውያን ቤት እድሳት፣ አቅመ-ደካሞችን እና ወላጅ አልባ ሕጻናትን በቋሚነት በመደገፍ አርዓያነት ያለው ተግባር እያከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
በተለይም በክልሉ ከነበረው የሰላም እጦት ጋር ተያይዞ የተፈተነውን የትምህርት ዘርፍ ለማገዝ፣ በሁሉም ቅርንጫፎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የማድረግ ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።
አቶ ታደለ አክለውም፣ ተተኪ ትውልድ ላይ መሥራት ሀገርን የመገንባት መሠረት በመኾኑ አሚኮ በቅርቡ ራሱን የቻለ የሕጻናት ቻናል ሥራ ለማስጀመር በትኩረት እየሠራ መኾኑን አስታውቀዋል።
በስጦታ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ኤፍ ኤም ደብረ ብርሃን 91 ነጥብ 4 ኀላፊ ይርጉ ፋንታ ሠራተኞቹ ያደረጉት ተሳትፎ ሌሎች ተቋማትን የሚያነሳሳ መኾኑን ገልጸዋል። የሠራተኞች ተወካይ ወይዘሮ ሔለን ተክሉ በበኩላቸው፣ ሠራተኛው በሙሉ ፍላጎት እና ተነሳሽነት በድጋፉ መሳተፉን ጠቅሰው የተቸገሩ ሕጻናት እና ወላጆች ደስ ብሏቸው ከማየት በላይ የህሊና እርካታ እንደሌለ ተናግረዋል።
የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ዋስዬ አሊ እና የተማሪ ወላጆች ትምህርት ቤቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልጆች የሚማሩበት በመኾኑ የተደረገው ድጋፍ ትልቅ ትርጉም ያለው መኾኑን ገልጸዋል። ለአሚኮ ሠራተኞችም ምሥጋና አቅርበዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ተወካይ መሠረት መንግሥቱም ለአሚኮ ሠራተኞች እና መሪዎች ምሥጋናቸውን አቅርበው ሌሎች ተቋማትም ይህንን በጎ ፈለግ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ሠራተኞች እና መሪዎች ያደረጉት ይህ ድጋፍ ተቋሙ ለትምህርት ዘርፉ እና ለተተኪው ትውልድ የሚሰጠውን ከፍተኛ ቦታ የሚያሳይ ተግባራዊ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
✍️ዘጋቢ፦ ሥነ ጊዮርጊስ ከበደ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሴቶች የክልሉን ሰላም ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ በንቃት ሊሳተፉ ይገባል።
Next articleያልተጠገነው የአማራ ቁስል እና አዲሱ የሕገወጡ ሕወሃት የጦርነት ሴራ