ሴቶች የክልሉን ሰላም ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ በንቃት ሊሳተፉ ይገባል።

6
🕊️
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አካላት በተገኙበት ሴቶች ለሰላም እና ደኅንነት በሚኖራቸው ሚና ዙሪያ መክሯል።
በግንዛቤ ምክክሩ ሴቶች በድርድር፣ በሽምግልና እና በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ሲኾኑ የሰላም ስምምነቱ ቢያንስ ለ15 ዓመታት ዘላቂ የመኾን ዕድሉ በ35 በመቶ እንደሚጨምር ተነስቷል።
በሰላም ውይይቶች ወቅት ሴቶች ከሥልጣን እና ከወንበር ሽሚያ ይልቅ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ እና የጉዳት ሰለባዎች ፍትሕ እንዲያገኙ ትኩረት ስለሚሰጡ ለፍትሕ እና ለሽግግር ፍትሕ አጀንዳዎች ስኬት ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ታምኖ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ መድረኩን አዘጋጅቷል ነው የተባለው።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አማካሪ ኮሎኔል ባምላኩ ዓባይ እንዳብራሩት ሴቶች በሰላም እና ደኅንነት ማስከበር ዙሪያ ያላቸው ተሳትፎ እጅግ ከፍተኛ ነው። ሰላም በሚታጣበት ጊዜም ሴቶች ለጾታዊ እና ለሌሎችም ጥቃቶች በስፋት ተጋላጭ እንደሚኾኑ ተናግረዋል።
ሴቶች እንደ እናት እና የቤተሰብ አሥተዳዳሪነታቸው በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰላምን በማስፈን ረገድ ያላቸውን ጉልህ ሚናም አንስተዋል። ይህንን መሠረት በማድረግም ከተለያዩ ተቋማት ለተወጣጡ አካላት የግንዛቤ መፍጠር ሥራ በስፋት እየተሠራ መኾኑን ኮሎኔሉ አስታውቀዋል።
የሰላም እና ደኅንነት ቢሮ ከሴቶች እና ሕጻናት ቢሮ ጋር በቅርበት እየሠራ መኾኑን እና ሥራውን ተቋማዊ ለማድረግ እየተሠራ ላለው ሥራ ማሳያ በማድረግ አንስተዋል።
ሴቶች በሰላም ግንባታ ያላቸውን የባለቤትነት ስሜት ለማጠናከር፣ ጥቃትን ለመከላከል እና ዳግም እንዳይከሰት ለማድረግ በሁሉም ተቋማት እስከ ታችኛው መዋቅር (ቀበሌ) ድረስ የሴት የደኅንነት መዋቅር የማቋቋም ሥራ መጀመሩንም አስታውቀዋል።
ሴቶች በሰላም እና ደኅንነት ዙሪያ የሚኖራቸውን ሚና ለማሳደግ ጠንካራ አደረጃጀት መፈጠሩንም ጠቁመዋል። በአብዛኛው የክልሉ ዞኖች እና ወረዳዎች ይህንን አደረጃጀት በመጠቀም የተሻለ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።
የሴቶች የሰላም ተሳትፎ ይበልጥ ውጤታማ እንዲኾን ሁሉም ተቋማት ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ሴቶችን ማበረታታት እና ከጎናቸው መቆም እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል።
ሴቶችም ራሳቸው ያላቸውን ትልቅ ድርሻ በመረዳት፣ ግንዛቤ ለሌላቸው ግንዛቤ በመፍጠር እና በመደራጀት የክልሉን ሰላም እና ደኅንነት ካለበት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበምዕራብ ጎጃም ዞን የተሰማራው መከላከያ ሠራዊት ሀገራዊ አደራውን በላቀ ጀግንነት እየተወጣ ነው።
Next articleአሚኮ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን በመወጣት ተተኪ ትውልድ ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።