
የምሥራቅ ዕዝ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል መላኩ ገላነህ በፀጥታ ማስከበር እና በግዳጅ ላይ የሚገኘውን ሠራዊት እየተዘዋወሩ ያለበትን የዝግጁነት ደረጃ ቃኝተዋል። አዛዡ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ሠራዊቱ የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ሕግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
አዛዡ፣ የምሥራቅ ዕዝ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና ሁሉ የተላላኪዎችን ሴራ በማምከን ድልን መቀዳጀት የተለየ መለያው እንደሆነ አስታውሰዋል።
የኮሩ የሠራዊት አባላት የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን ደህንነት በመጠበቅ ሰላም አስተማማኝ ከማድረግ አንፃር እያከናወኑት ያለው ግዳጅ ውጤታማ መሆኑን አዛዡ አረጋግጠዋል።
ኮሩ ትልቅ አሀድ እንደመኾኑ መጠን በተሰጠው ተልዕኮ ሁሉ ትልልቅ ድሎችን እና ታሪካዊ ስኬቶችን ማስመዝገቡን እየቀጠለ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
የቀደሙት አባቶቻችን በደምና በአጥንት ዋጋ ከፍለው ያቆዩልንን ሀገር፣ እኛ የዛሬዎቹ ትውልዶች ነፃነቷን እና ሉዓላዊነቷን አጽንተን በማስጠበቅ ሀገራዊ አደራችንን በብቃት መፈፀም አለብን ብለዋል።
ጄኔራል መኮንኑ፣ ኮሩ የባዕዳንን ረጅም የጥፋት ዕጅ በመቆራረጥ የተጣለበትን ታሪካዊና ሀገራዊ አደራ ከክልሉ የፀጥታ ኃይል ጋር በመጣመር በውጤታማነት መወጣቱን እንደሚቀልጥ አረጋግጠዋል።
የሠራዊቱ አባላት በላቀ የሥነ ልቦና ዝግጅት፣ በጽናትና በወታደራዊ ዲሲፕሊን በመታነፅ የሕዝብ እና የመንግሥትን አደራ እስከ መጨረሻው በድል አድራጊነት እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
ዘገባው የምሥራቅ ዕዝ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
