የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ እና የዘላቂ ኢኮኖሚ ህልውና

7
🌱🌳
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከተራ የችግኝ ተከላ ዘመቻነት በመሻገር የሀገርን ሕልውና፣ የምግብ ዋስትናን እና ኢኮኖሚያዊ ነፃነትን የሚያረጋግጥ ጥልቅ ሀገራዊ “የአረንጓዴ አብዮት” ደረጃ ላይ ደርሷል። መርሐግብሩ የተራቆተ የተፈጥሮ ሀብትን መልሶ ከማከም ባለፈ፣ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት፣ የቡና እና የፍራፍሬ ልማትን በማስፋት ዓለም አቀፍ ገበያን የተቀላቀለበት እና የውጭ ጥገኝነትን በዘላቂነት ለመስበር የሚያስችል ዘመናዊ የልማት አውድ ፈጥሯል።
ዕውነተኛ ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው በድንበር ጥበቃ እና በጦር መሳሪያ ብልጫ ብቻ ሳይኾን ሕዝብን በራስ አቅም መመገብ እና ኢኮኖሚያዊ ነፃነትን ማረጋገጥ ሲቻል ነው። መሬትን በማልማት እና የግብርና ሥርዓቱን በማዘመን የሚከናወነው ይህ ንቅናቄ የውጭ እርዳታን እና የፖለቲካ ተጽዕኖን ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት እየጣለ ይገኛል። ታዋቂው ባለሀብት ዋረን ቡፌት “ዛሬ አንድ ሰው በጥላ ሥር ተቀምጦ የሚያርፈው ከረጅም ጊዜ በፊት ሌላ ሰው ዛፍ ተክሎ ስለነበር ነው” እንዳሉት፣ ዛሬ በጋራ የሚፈሰው ላብ እና የሚተከለው እያንዳንዱ ችግኝ የነገዋ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል፣ በአየር ንብረት ለውጥ እንዳትበገር እና በዓለም አቀፍ መድረክ አንገቷን ቀና አድርጋ እንድትራመድ የሚያደርግ የሉዓላዊነት የጀርባ አጥንት ነው።
ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በጋራ የተሰለፉበት ይህ ንቅናቄ ልዩነቶችን አቻችሎ ሕዝብን በአንድ ዓላማ ሥር ያሰለፈ የብሔራዊ አንድነት እና የአብሮነት ማሳያ ኾኗል። ኬንያዊቷ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ እና የአረንጓዴ ቀበቶ መሥራች ዋንጋሪ ማታይ “ዛፍ ስንተክል የሰላምን እና የተስፋን ዘር ነው አብረን የምንዘራው” እንዳሉት ሁሉ፣ በየዓመቱ የሚከናወነው ይህ አረንጓዴ አሻራ የተስፋ እና የሰላም ዘርን በሀገሪቱ ምድር ላይ የመዝራት ሂደት ነው።
“አፈሯን የምታወድም ሀገር ራሷን ታጠፋለች፤ ደኖች የሀገራችን ሳንባዎች ናቸው” በማለት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዲ.ሩዝቬልት የተናገሩት አባባል ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ሕያው ትርጉም አግኝቷል። በጥንታዊ ግሪካውያን ዘንድ “አንድ ማኅበረሰብ ታላቅ የሚኾነው አዛውንቶች መቼም ጥላው ስር እንደማይቀመጡ እያወቁ ዛፍ ሲተክሉ ነው” እንደሚባለው፣ የአረንጓዴ አሻራም ከራስ ወዳድነት የጸዳ፣ የአሁኑ ትውልድ ለቀጣዩ የሚያወርሰው የብልጽግና አደራ ነው። ይህ የኢትዮጵያውያንን አይበገሬነት ዳግም ያረጋገጠ እና ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች፣ አረንጓዴ እና ሉዓላዊነቷ የተከበረች ሀገርን ለማስረከብ የሚደረግ የዘመናችን ደማቅ የታሪክ ምዕራፍም ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሀገር የሚለማው እና የሚገነባው በተማረ ዜጋ ነው።
Next articleበምዕራብ ጎጃም ዞን የተሰማራው መከላከያ ሠራዊት ሀገራዊ አደራውን በላቀ ጀግንነት እየተወጣ ነው።