ሀገር የሚለማው እና የሚገነባው በተማረ ዜጋ ነው።

14
የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በምሥራቅ ጎጃም ዞን በጎዛምን ወረዳ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር ከ300 በላይ ለሚኾኑ ሕጻናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
ኮሚሽኑ በመርሐ ግብሩ የችግኝ ተከላ፣ ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎች የቤት ግንባታ እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ በጎ ፈቃድ ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡
የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ ሀገር የሚለማው እና የሚገነባው በተማረ ሰው መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡
የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን መደገፍ ሀገርን መገንባት መኾኑንም አስረድተዋል፡፡
ተቋሙ በአካባቢው የጀመራቸውን የበጎ ፈቃድ ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ በበኩላቸው ዞኑ በትምህርት ዘርፍ በርካታ ምሁራንን ያፈራ ቢኾንም በግጭት ምክንያት በዘርፉ ላይ ስብራት መፈጠሩን ገልጸዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ኮሚሽኑ ላደረገው ድጋፍ እና ትብብርም ምሥጋና አቅርበዋል።
የአካባቢው ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱን የጠቀሱት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በአካባቢው ላከናወነው የበጎ ፈቃድ ሥራ ምሥጋና አቅርበዋል።
ተማሪዎቹ በበኩላቸው የተደረገላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለትምህርታቸው አጋዥ መኾኑን ጠቅሰው ለዚህም ምሥጋና አቅርበዋል።
ድጋፉ ትምህርታቸውን በትጋት ለመከታተል ተጨማሪ መነሳሳት እንደሰጣቸውም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከሀገር ሉዓላዊነት እስከ ዓለም አቀፍ የሰላም አምባሳደርነት !
Next articleየኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ እና የዘላቂ ኢኮኖሚ ህልውና