ከሀገር ሉዓላዊነት እስከ ዓለም አቀፍ የሰላም አምባሳደርነት !

19

 

የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ደኅንነት ከማስከበር ባለፈ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታመን የሰላም አምባሳደር ኾኖ ዘልቋል።

ሠራዊቱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በተሰጡት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የኢትዮጵያን ሀገራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ገጽታ ከፍ ያደረገ የደማቅ ታሪኮች ባለቤት ነው።

በሰላም ማስከበር ሥራው ባሳየው ፈጣን ምላሽ እና ወታደራዊ ሥነ-ምግባር አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አክብሮትን አትርፏል።

ታሪካዊ የሰላም ተልዕኮዎች እና የደመቁ አሻራዎች፦

በኮሪያ ዘመቻ በፍጹም የውጊያ ብቃት እና ጀግንነት ዓለምን ያስደመመበት አጋጣሚ ሲኾን በተለይም አንድም ምርኮኛ ለጠላት አሳልፎ አለመስጠቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ሥነ-ምግባሩን ያስመሰከረ እንደኾነ ይነገርለታል።

በኮንጎም ቢኾን ሀገሪቱ ከነጻነት ማግስት የገጠማትን የፖለቲካ አለመረጋጋት ለማስወገድ ከተባበሩት መንግሥታት የተሰጠውን ተልዕኮ በስኬት ተወጥቷል።

በሩዋንዳ በነበረው አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ወንጀል ወቅት መሃል በመገኘት የሺዎችን ሕይወት ታድጓል፤ በሩዋንዳ ሕዝብ ዘንድም እስካሁን የሚታወስ ታላቅ የሰብዓዊነት ውል ውሏል።

በአወዛጋቢው በአብዬ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን የድንበር ግጭት ወቅትም ገለልተኛ፣ ታማኝ እና እውነተኛ የሰላም አስከባሪነቱን በተግባር አሳይቷል።

በሱማሊያ የቀጣናውን ሰላም ያናጋውን አል-ሸባብን በመዋጋት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ ቁልፍ ከተሞችን ነጻ አውጥቷል፤ የመንግሥት መዋቅር እንዲጠናከር እና መረጋጋት እንዲሰፍንም አድርጓል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት
ዛሬም እንደ ትላንቱ “የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍትሔ የማስገኘት” መርህን በመከተል በጀግንነቱ እና በግብረ-ገብነቱ ለቀጣናው እና ለዓለም ሰላም አስተማማኝ አለኝታነቱን እያስመሰከረ ይገኛል።

ከውስጥም ኾነ ከውጭ የሚቃጡ ማናቸውንም የደኅንነት ስጋቶች እና ጥቃቶች በብቃት በመመከት የሀገሪቱን አንድነት እና ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ እየጠበቀ ይገኛል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የልዩ ዘመቻዎች ኮማንዶ 65ኛው ዓመት በዓል በተከበረበት ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ የሰላም ምንጭ እንጂ የማንም ሀገር ወራሪ ኾና አታውቅም፤ ወደፊትም አትኾንም ብለዋል።

ሆኖም ግን የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚጋፋ እና ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተን ማንኛውም ኃይል ሠራዊቱ በደረሰበት የላቀ የዝግጁነት ደረጃ እና በታጠቀው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተመጣጣኝ እና የማያዳግም ምላሽ ለመስጠት በተሟላ ቁመና ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

ይህ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል እና በጠንካራ አመራር የተገነባው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አሁን ላይ የቀጣናው የሰላም ዋስትና እና የማይናወጥ የሀገር ሉዓላዊነት ዓምድ ኾኗል።

በአጠቃላይ የተመዘገቡት እነዚህ ሁለንተናዊ ስኬቶች የሚያረጋግጡት አንድ እውነት አለ፤ እርሱም ሠራዊታችን ዛሬ ላይ የቴክኖሎጂ የበላይነትን የታጠቀ፣ በወታደራዊ ዲሲፕሊን የታነጸ እና ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ የሕዝብ አለኝታ መኾኑን ነው።

#አሚኮ_ዜና #EthiopianDefenseForces🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_01_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በምሥራቅ ጎጃም ዞን የችግኝ ተከላ እና ለአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት ግንባታን አስጀመረ።
Next articleሀገር የሚለማው እና የሚገነባው በተማረ ዜጋ ነው።