
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች በምሥራቅ ጎጃም ዞን ጎዛምን ወረዳ በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብር በመሳተፍ የችግኝ ተከላ እና አቅም ለሌላቸው ወገኖች የመኖሪያ ቤት ግንባታን አስጀምረዋል።
መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ እንደገለጹት በየዓመቱ የሚከናወነው የክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራ በተቋሙ የዳበረ ባሕል ነው። ኮሚሽነሩ አክለውም በዕለቱ የተተከሉት የአቮካዶ እና የቡና ችግኞች ዘላቂ ውጤት እንዲያስገኙ ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
በዚሁ መርሐ ግብር ለአቅም ደካሞች እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች የሚኾኑ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የተጀመረ ሲኾን ቤቶቹ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው ለተጠቃሚዎች እንደሚተላለፉ ተገልጿል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ያሳየውን የበጎ ፈቃድ ተነሳሽነት አድንቀው በዞኑ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎችም ዘርፎች የሚከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ታሪኩ ዳኘ ኮሚሽኑ የሕግ ታራሚዎችን ከመጠበቅ ተልዕኮው ባሻገር ለማኅበረሰቡ ያለውን የልማት አጋርነት በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።
በዕለቱም የፌዴራል እና የአካባቢው መሪዎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
