የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገር የሚጠብቅ ብቻ ሳይኾን አምራች ኀይልም ነው።

22

 

የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ሀገር የሚጠብቅ ብቻ ሳይኾን አምራች ኀይል መኾኑን የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የግብርና ልማት ተሞክሮ አሳይቷል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች “ጳጉሜን 1 የዕመርታ ቀን” በሚል መሪ መልዕክት በሰሜን ምዕራብ ዕዝ ባሕር ዳር በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ በግብርና ዘርፍ እያከናወናቸው የሚገኙ ልማቶችን ጎብኝተዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ግብርና ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ዓለም ውልጫፎ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገርን ከመጠበቅ ባሻገር በተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተሳተፈ ይገኛል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ “ምግባችን ከቤታችን” በሚል በዕዙ መሥሪያ ቤት የተለያዩ የግብርና ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል።

ዕዙ በመሥራያ ቤቱ ግቢ ውስጥ 28 ሄክታር ማሣ በበቆሎ መሸፈኑን ገልጸዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ የሥጋ እና የእንቁላል ዶሮዎችን እና የወተት ላሞችን በማራባት እንዲኹም ንብ በማነብ ለሠራዊቱ ምግብ ከማቅረብ ባሻገር ለአካባቢው ማኅበረሰብም በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዕዙ በዚህ የምርት ዘመን ከፍተኛ የበቆሎ ምርት ለማምረት ማቀዱን የጠቆሙት ኮሎኔሉ የግብርና ሥራው ሠራዊቱ ሀገር ከመጠበቅ ባሻገር አምራች ኀይል መኾኑን ያሳየበት ነው ብለዋል።

በግብርና ሥራው ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል እየተፈጠረ መኾኑንም ነው የተናገሩት።

የባሕር ዳር ከተማ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ኀይለማርያም እሸቴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገር እየጠበቀ እና እያቀና የሚገኝ ሠራዊት ነው።

ከዚህ ባሻገር ሠራዊቱ ወደ ምርት በመግባት ኢትዮጵያ ራሷን ለመቻል የጀመረችውን ጥረት የሚደግፍ ተግባር እያከናወነ መኾኑን ከወሬ ባሻገር በተግባር ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

ሌሎች ተቋማት የሠራዊቱን ተሞክሮ ወስደው በዚህ ልክ መሥራት ቢችሉ እንደ ሀገር የተያዘውን ዕቅድ በአጭር ጊዜ ማሳካት ይቻላል ነው ያሉት።

በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና በሌሎች ጾም የሚያድሩ መሬቶችን ወደ ምርት ማስገባት እንደሚገባ ያየንበት ነውም ብለዋል።

የዕመርታ ቀን ሲከበር የታዩ ተሞክሮዎችን በመውሰድ እና በየደረጃው በመተግበር እንደ ሀገር የተያዘውን የዕድገት እና የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የድርሻን መወጣት ይጠበቃል ነው ያሉት።

የክልሉ እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች በከተማዋ እየተገነቡ የሚገኙ ሸዶችን፣ በኢንተርፕራይዞች እና በግለሰቦች እየተከናወኑ የሚገኙ የዶሮ እርባታ እና የእንሰሳት ማድለብ ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

#Ameco #Ethiopiadefenceforce #Ethiopia🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_01_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበዞኑ 14 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።
Next article“የኢትዮጵያን ትንሣኤ ወደ ዘላቂ ብልጽግና ከፍ እናደርጋለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)