በዞኑ 14 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።

16

 

የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ በግብርናው ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በጉብኝት በመቃኘት «የዕመርታ ቀንን» በፍኖተ ሰላም ከተማ አክብሯል።

የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንገሻ እንኳኾነ እንደገለጹት በከተማ አሥተዳደሩ ምርት እና ምርታማነትን የሚያሳደጉ ሥራዎች ተጠናክረው እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ሰብልን በመኸር ወቅት ከማልማት ባለፈ ያሉትን ፀጋዎች በመጠቀም በበጋ መስኖ የማልማት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየቱንም አብራርተዋል።

አክለውም የቡና እና ፍራፍሬ ልማትን ወደ ሰፊ የኩታ ገጠም አሠራር ለማሳደግ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው የምግብ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅም ሳይታረሱ የቆዩ ከ31 ሄክታር በላይ የቆዩ መሬቶች መልማታቸውን ተናግረዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሰውመኾን ተገኘ በበኩላቸው የግብርናውን ዘርፍ ከነበረበት ኋላቀር አሠራር ለማውጣት የክላስተር አደረጃጀቶችን የማጠናከር እና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አማራጮችን የመጠቀም ሥራዎች ትኩረት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በመኸር ወቅት ከሚለማው ከ266 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በተጨማሪ ጾም ሲያድሩ የነበሩ መሬቶችን በሰብል የመሸፈን ውጤታማ ተግባር መከናወኑንም አንስተዋል።

ኀላፊው አክለውም በዞኑ ባለፈው ዓመት ከተገኘው 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በዘንድሮው የምርት ዘመን ወደ 14 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በጉብኝቱ የተሳተፉ አካላት በሰጡት አስተያየት ዘመናዊ ግብርናን እውን ለማድረግ እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ እንቅስቃሴዎች የሚያበረታቱ መኾናቸውን ገልጸዋል።

#አሚኮ #ምዕራብጎጃም #ግብርና #የምግብሉዓላዊነት #አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ፍኖተ_ሰላም #ጳጉሜን_01_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ንጉሥ ስንታየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ተቋማዊ ሪፎርም በመሥራት የክልሉን ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይኖርበታል” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleየሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገር የሚጠብቅ ብቻ ሳይኾን አምራች ኀይልም ነው።