“ዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ተቋማዊ ሪፎርም በመሥራት የክልሉን ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይኖርበታል” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

17

 

የዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ግምገማ፣ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ እና የማጽደቅ መረሐ ግብር በሎጎ ሐይቅ ሪዞርት እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና የዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የቦርድ ሠብሣቢ አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት ኢንቨስትመንት ሆልዲንጉን በመደገፍ፣ በማጠናከር እና ውጤታማ በማድረግ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ዘላቂ ሃብት እና ጥሪት ያለው ጠንካራ ኩባንያ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።

የዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የክልሉን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማረጋገጥ ዋና ዓላማው መኾኑን የጠቆሙት ዶክተር አብዱ ሁሴን በተቋማት አደረጃጃት እና አሠራር፣ በሪፎርም አተገባበር እና በፋይናንስ አሠራር፣ በላቀ የፕሮጀክት አፈጻጸም እና በሌሎችም ሥራዎች የተገኙ ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ገልጸዋል።

በቀጣይ የሥራ ዘመን በኩባንያዎች ሪፎርም መሥራት የዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ቀዳሚ ተግባር እንደሚኾንም አመላክተዋል። ዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሪፎርም በመሥራት የክልሉን ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይኖርበታልም ብለዋል::

ሃብትን መያዝ ብቻውን የስኬት መገለጫ አይደለም ያሉት ዶክተር አብዱ ሁሴን በፍጥነት እና በከፍተኛ ምጣኔ የሚያተርፍ ኩባንያ መገንባት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ይህን ግብ ለማሳካት ደግሞ የለውጥ ጉዞን መመርመር እንደሚያስፈልግ ያመላከቱ ሲኾን የተደበላለቀ የኩባንያዎችን አሠራር እና ውጤታማነት ለማሻሻል አዳዲስ የኮርፓሬት ባሕልን መላመድ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

በዓባይ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የሚገነባው የኩባንያ ሥርዓት ለትውልድ የሚሸጋገር ሃብት መኾኑንም ተናግረዋል።

የዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ታደሠ ካሳ (ዶ.ር) በሰባት የኢንቨስትመንት ዘርፎች 46 የተለያዩ ኩባንያዎች እንዳሉ አመላክተዋል።

የዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በቀጣይ ድርጅታዊ ሪፎርም በማከናወን፣ የሰው ኀይሉን በማጠናከር፣ ዲጂታላይዜሽንን በመተግበር እና የአዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

የአፈፃፀም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረኩ ዝቅተኛ አፈጻጻም ያስመዘገቡ ውስን ኩባንያዎች የተሻለ አሠራር እና አፈፃፀም ካላቸው ልምድ በመውሰድ ወደ ተቀራራቢ ደረጃ የሚሸጋገሩበት እንደሚኾንም አንስተዋል።

በቀጣይ ቀናት ኩባንያዎች በተናጠል ከዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2019 ዕቅድ እንደ ሚያፀድቁ የወጣው መርሐግብር ያስረዳል።

በግምገማ መድረኩ የዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ መሪዎች፣ የኩባንያዎች ሥራ አሥፈፃሚዎች እና የቦርድ አባላት እየተሳተፉ ነው።

#አሚኮ #ዓባይኢንቨስትመንትሆልዲንግ_ተቋማዊ_ሪፎርም #አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ደሴ #ጳጉሜን_01_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ጀማል ይማም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበአንድ ዓመት ብቻ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ። 🇪🇹
Next articleበዞኑ 14 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።