“የታሪክ ተወቃሽ ላለመኾን ከጓደኞቼ ጋር የሰላም አማራጭን ተቀብያለሁ” ብሬኑን ይዞ ሰላምን የመረጠው ወጣት

11
በሰሜን ጎንደር ዞን የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች የሰላምን አማራጭ በመቀበል በአዲስ ዓመት ዋዜማ ለሕዝቡ የሰላም ስጦታ እያበረከቱ ነው።
በክልሉ የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ለ11 ዓመት አገልግሏል። በ2015 ዓ.ም ደግሞ ጥያቄዎችን በአፈሙዝ እናስፈታለን በሚል ወደ ጫካ መግባቱን ያስታውሳል።
በሰሜን ጎንደር ዞን ሲንቀሳቀሱ በቆዩ ታጣቂዎች የሻለቃ መሪ ነበር አምሳያው ገብሬ። በሕዝብ ላይ እገታ፤ ዘረፋ እና የተለያዩ በደሎችን ታጣቂ ኃይሎች ሲፈጸሙ በመታዘቡ ከትግሉ መውጣቱን ለአሚኮ ዲጂታል ተናግሯል።
የአማራን ሕዝብ ነጻ አወጣለሁ ብሎ ጫካ የወጣ የታጣቂ ኃይል ከአማራ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ሢሠራ በመመልከቱ የታሪክ ተወቃሽ ላለመኾን ከጓደኞቹ ጋር ብሬን ይዞ ከትጥቅ ትግል መውጣቱን ገልጿል።
“በአዲስ ዓመት ለማኅበረሰቡ ሰላምን ለመስጠት የሰላም አማራጭ ተቀብለናል”ነው ያለው። ጥያቄዎችን በአፈሙዝ ለመመለስ ከመታገል ይልቅ በሃሳብ ማሸነፍን ማስቀደም እንደሚገባ ተናግሯል። በቀጣይ በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ የበኩሉን እንደሚወጣም ገልጿል።
የደባርቅ ወረዳ ሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ሽፈራው ኪሮስ የሀገር ሽማግሌዎችን፤ የሰላም ካውንስልን፤ የሰላም እናቶችን እና ማኅበረሰቡን በማደራጀት ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ተሠርቷል ብለዋል።
ከማኅበረሰቡ ጋር በቅንጅት በመሠራቱ ታጣቂዎች የሚያደርሱትን ጉዳት እንዲገነዘቡ፤ የሰላምን ጠቀሜታ እንዲረዱ በማድረግ በ2018 ዓ.ም በርካታ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ መቀበላቸውን ገልጸዋል።
የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎች በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎችን በመምከር እየመለሱ መኾኑንም ተናግረዋል። ግጭቱ በማኅበረሰቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል።
ወረዳው የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎችን በተሃድሶ ሥልጠና እንዲያልፉ በማድረግ መልሶ ለማቋቋም መሠራቱን ነው የተናገሩት። በቀጣይ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ በትኩረት ይሠራል ያሉት ምክትል ኀላፊው የሰላም አማራጭን በማይቀበሉ ታጣቂዎች ላይ ሕግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ ከሰሞኑ ከሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰላምን ዋጋ የምንረዳው እንደ ጤና ስናጣው ነው ብለዋል። ሕዝቡ ቅድሚያ ለሰላም ዋጋ በመስጠት ከመንግሥት ጋር በመኾን ሰላምን ለማጽናት እየሠራ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
በቀጣዩ ዓመት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲሄዱ፤ ገበሬው ምርቱን እንዲሠበሥብ፤ ነጋዴዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዲነግዱ፤ ዜጎች በየቦታው በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ ሁሉም የበኩሉን ሚና በመወጣት ሰላምን በአዲሱ ዓመት እንዲያጸናም አሳስበዋል።
ችግሮች እያለፉ የኢትዮጵያ ብርሃን እየተገለጠ መጥቷል ነው ያሉት። ሰላምን ማጽናት፤ ጥላቻን ማስወገድ፤ ጥላቻን የሚዘሩ አካላትን በቃችሁ ማለት፤ በደል እና ቁርሾን ከማንሳት ይልቅ ይቅር ባይነትን ማስቀደም በአዲሱ ዓመት ከሕዝቡ የሚጠበቅ ተግባር መኾኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበቴክኖሎጂ የተቃኘው የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ!
Next articleባሕርዳር የኢትዮጵያን የስኬት ጉዞ እያሳየች ነው።