
ዛሬ ላይ ቴክኖሎጂ የቅንጦት ጉዳይ አይደለም። የሀገራት ብሔራዊ ደኅንነት፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ መለኪያ ወደ መኾን ተሸጋግሯል። ኢትዮጵያም ይህንን በመረዳት ጉዞዋን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ አድርጋለች።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን አቅም በተግባር እያረጋገጠች እና ለአፍሪካ ኢኖቬሽን መንገድ እየጠረገች ትገኛለች ብለዋል።
ሀገሪቱ አሁን ለደረሰችበት የቴክኖሎጂ ጉዞ ግን መንገዱ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ከጥቂት ዓመታት በፊት ሀገሪቱ በዘርፉ በርካታ መዋቅራዊ ማነቆዎች ነበሩባት። የቴሌኮም ዘርፉ በአንድ የመንግሥት ተቋም ስር ብቻ በመቆየቱ የኢንተርኔት ተደራሽነት እና ጥራት እጅግ ዝቅተኛ ነበረ።
የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩም የፋይናንስ ዘርፉ በወረቀት ላይ የተመሠረተ ኾኖ ቆይቷል። ለፈጠራ ሥራዎች የሚኾን ምቹ ሥነ-ምህዳር እና የላቁ ቴክኖሎጂዎችን የሚመሩ ተቋማት አለመኖራቸውም ሀገሪቱን ከዓለም አቀፉ የዲጂታል አብዮት አግልሏት ቆይቷል።
በቅርብ ጊዜ የተወሰዱ የሪፎርም ርምጃዎች ግን ይህንን የዝግመት አዙሪት ሰብረው ተጨባጭ ውጤቶችን እያሳዩ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሳይንስ ሙዚየምን ሲመርቁ፣ “ትላንት ሌሎች የፈጠሩትን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ነበርን፤ ዛሬ ግን የራሳችንን አቅም ገንብተን የነገዋን ታላቅ ኢትዮጵያ በራሳችን ልጆች እጅ እንቀርጻለን” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት እና አዲስ የኤ.አይ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋምን ጨምሮ በግዙፍ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጅማሮዎች አማካኝነት ወጣቶቿን ለወደፊቱ በማዘጋጀት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ኾናለች” በማለት የሀገሪቱን ራዕይ መስክረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
