“ከተዘጉ ፋብሪካዎች ወደ ምርት ትንሣኤ”

17
ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ከባሕላዊ ምርት ወደ ዘመናዊ ተወዳዳሪ ማኑፋክቸሪንግ በመሸጋገር ለውጥ እያስመዘገበች እና እያንሠራራች ትገኛለች።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከማስፋፋት ባለፈ የጨርቃ ጨርቅ፣ የሲሚንቶ፣ የቆዳ፣ የሌጦ እና ሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፎች የማምረት አቅም እያደገም መጥቷል። ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድልም ፈጥሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “የኢትዮጵያ ታምርት” እንቅስቃሴዎች ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ስር ነቀል በኾነ መልኩ በመቀየር ላይ ናቸው ማለታቸው የሚታወስ ነው። ሀገሪቱ በሰፊው ወደ አምራችነት በማሸጋገር ላይ ትገኛለችም ብለዋል። በተለይም ፈተናዎችን አልፎ በተተገበረው ሪፎርም አስደናቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደኾነም ገልጸዋል።
የዚህ ስኬት የኢንዱስትሪ ልማቱ ከመንግሥት መር ወደ ግል ዘርፍ እንዲሸጋገርም ተደርጓል ነው ያሉት። ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በመተካትም የውጭ ምንዛሬን ማዳን ተችሏል፤ በዚህም ከውጭ ይገባ የነበረውን የስንዴ ግዥ እና ለቢራ ብቅል ይወጣ የነበረውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።
የምርት አቅምን አሟጦ የመጠቀም ሥራ ተሠርቷል። በዚህም ተዘግተው የነበሩ በርካታ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ተመልሰዋል፤ የፋብሪካዎች የማምረት አቅም ከነበረበት 47 በመቶ ወደ 67 መቶ አድጓል። የሀገር ውስጥ የፍጆታ ምርቶች ድርሻም በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አንስተዋል።
የሀገሪቱ የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) አፈጻጸምም ከፍተኛ እድገት አሳይቷል ነው ያሉት። የውጭ ምንዛሬውም ከሦስት ዓመት በፊት ከነበረበት በእጥፍ አድጓል ብለዋል።
ሪፎርሙ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን እግር ከወርች ቀይዷት ከነበረው ውስብስብ ችግር ወጥታ ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ከፍታ እየተጓዘች መኾኗን በግልጽ የሚያሳይ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንደገለጹት ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የማንፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉ የኢኮኖሚ ድርሻውን ከፍ ለማድረግ እና ተወዳዳሪነቱን ለማረጋገጥ ሰፊ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች። በኢንዱስትሪዎች ላይ የነበሩ ማነቆዎችን በመፍታት ለዘርፉ ትንሣኤ ማረጋገጫ ኾነዋል ብለዋል።
የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ከዚህ ቀደም አንድ በመቶ ብቻ የነበረው የብድር ድርሻ ወደ 5 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ማለት ችሏል ነው ያሉት። በየዓመቱ ወደ ምረት የሚገቡ አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል።
የኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነት፣ ምርታማነት እና ትርፋማነትም እያደገ ይገኛል። የሀገራችንን የንግድ ሚዛን በማሳደግ፤ ዘላቂነትን እና ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ አዳዲስ የገበያ አማራጮችን ያካተተ አዲስ የኤክስፖርት ስትራቴጂዎችም እየተለመዱ ይገኛሉ።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከጋሻ እስከ ሰው አልባ ድሮን – የመከላከያ ሠራዊት የማንሠራራት ጉዞ
Next articleበቴክኖሎጂ የተቃኘው የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ!