ባሕርዳር የኢትዮጵያን የስኬት ጉዞ እያሳየች ነው።

6
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “የኢትዮጵያ ማንሠራራት” በሚል መሪ መልዕክት ጳጉሜን ሁለት “የማንሠራራት ቀንን “በከተማው የተሠሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በመጎብኘት አክብሯል። ጉብኝቱም በዘመናዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የታጀበ ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ኢትዮጵያ ትላልቅ የልማት ሥራዎችን በማከናወን የትንሣኤ ጉዞ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ባሕር ዳር ከተማ ከኮሪደር ልማት ባሻገር በጣና ዳር የልማት ሥራዎች እያበበች፣ ሰላሟ እየተረጋገጠ እና የቱሪዝም ኢንቨስትመንቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል። ይህም እንደ ሀገር የገባነውን ቃል በተግባር የተፈጸመበት ነው ብለዋል። ከተማዋ የኢትዮጵያን የትንሳኤ ጉዞ እያሳየች መኾኗንም አንስተዋል። በከተማዋ የተጀመረው ሁለገብ ልማት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻሉን ገልጸዋል። ይህም የልማት እና የማንሠራራት ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
በተለይም የትራንስፖርት ዘርፍ አካላት እና ማኅበረሰቡ የከተማዋ አምባሳደሮች በመኾን ስለ ባሕር ዳር ሰላም፣ ውበት እና መልካም ገጽታ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ጎብኝዎች መናገር ይገባቸዋል ነው ያሉት። ማንሠራራት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃልም ብለዋል።
መከፋፈልን በመቃወም በአንድነት እና በመከባበር ጸንቶ መቆም እንደሚገባ ገልጸዋል።
በከተማው የብሩህ ተሥፋ የኤሌክትሪክ ባጃጆች ማኅበር ሠብሣቢ ወለላው አማረ በመርሐ ግብሩ በመሳተፋቸው ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል። በከተማው የተጀመሩት ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የልማት ማንሠራራት ማሳያ ናቸው ብለዋል። በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ የኤሌክትሪክ ባጃጆች ሐሙስ የበዓል ዋዜማ ዕለት ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡም አንስተዋል።
ሌላኛዋ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ የሺመቤት መርሻ የተሠሩ የልማት ተግባራት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው ነው ያሉት። በተለይም የኮሪድር ልማቱ ለነዋሪዎች ምቹ ነው ብለዋል። የጭስ አልባ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች መጀመርም የማኅበረሰቡን ችግር የፈቱ ውጤታማ ተግባራት መኾናቸውን አንስተዋል። ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የታሪክ ተወቃሽ ላለመኾን ከጓደኞቼ ጋር የሰላም አማራጭን ተቀብያለሁ” ብሬኑን ይዞ ሰላምን የመረጠው ወጣት
Next article“ኢትዮጵያም በተግባር እያንሠራራች ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ