ያልተጠገነው የአማራ ቁስል እና አዲሱ የሕገወጡ ሕወሃት የጦርነት ሴራ

8
❌
በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ታሪካችን ውስጥ ለአንዲት ሀገር ህልውና እና ለአዝማች ሕዝቦቿ አብሮ መኖር መሠረቱ እኩልነት፣ ፍትሕ እና እውነተኛ ወንድማማችነት ናቸው።
ኾኖም ግን ባለፉት ሦሥት አሥርት ዓመታት ሕገወጡ ሕወሃት በሕዝቦች መካከል የዘራው የብሔር እና የዘር ከፋፋይነት እንዲሁም በአማራ ሕዝብ ላይ ያደረሰው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጠባሳ አሁንም ድረስ አልተጠገነም።
የሕወሃት የጥላቻ ጉዞ የተጀመረው ገና በጫካ ትግሉ ወቅት ነበር። አማራውን የብሔሮች ሁሉ “ቀደምት ጨቋኝ” አድርጎ በመፈረጅ የተጻፈው ስሁት ትርክት ድርጅቱ ወደ ሥልጣን ሲመጣም የሀገሪቱ የፖለቲካ እና የትምህርት ሥርዓት ማዕከል እንዲኾን ተደረገ። ይህ ሥልታዊ ማግለል አማራው በገዛ ሀገሩ ባለቤትነት እንዳይሰማው እና በየቀኑ የሥነ-ልቦና ጫና እንዲሸከም አድርጎታል።
የታሪክ ሽሚያ፣ የመሬት ወረራ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቡድኑ የሥልጣን ኮርቻውን ከተቆናጠጠ በኋላም ታሪካዊ እና ሕዝባዊ ማንነታቸውን በመካድ የወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት እና የራያ አካባቢዎችን በኀይል እና በማጭበርበር ወደ ትግራይ ክልል አጠቃሎ ነበር።
በእነዚህ ቀጣናዎች ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች በማንነታቸው ብቻ ለሞት፣ ለእስራት እና ለአሰቃቂ መፈናቀል ተዳርገዋል፤ ባሕላቸውን እና ቋንቋቸውን እንዳያንጸባርቁም በግፍ ተከልክለው ነበር።
በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጆች ጥቃት ሲሰነዘርባቸው እና ሲፈናቀሉ መንግሥታዊ ከለላ ተነፍገው ነበር።
እንዲያውም በሥልታዊ የሕዝብ ቁጥር ቅነሳ ተሞክሮዎች በሴራ በተተበተቡ የቤተሰብ ምጣኔ ፕሮግራሞች እና ሕዝብ እና ቤት ቆጠራዎችን በማጭበርበር ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍን ፈጽሟል።
ሕገወጡ ሕወሃት የአማራን ክልል በልማት ወደኋላ ለማስቀረት ያላደረገው ጥረት አልነበረም። የኢንዱስትሪ፣ የመንገድ፣ የጤና እና የትምህርት ተቋማት ግንባታ ከክልሉ የሕዝብ ብዛት እና ስፋት ጋር ፈጽሞ የማይመጣጠን እንዲኾን አድርጎ ነበር።
አርሶ አደሮች በኢኮኖሚ እራሳቸውን እንዳይችሉ የመሬት ይዞታን እና የማዳበሪያ አቅርቦትን እንደ ፖለቲካዊ ማስፈራሪያ ይጠቀሙበት ነበር። ባለሀብቶች እና ነጋዴዎች ደግሞ በከባድ ታክስ እና በንግድ ፈቃድ ክልከላ ከገበያ እንዲወጡ ተደርገው ነበር።
ይህ ሁሉ ግፍ ሳያንስ በ2013 ዓ.ም ሕገወጡ ሕወሃት የለኮሰው ጦርነት ወደ አማራ ክልል (ወሎ፣ ጎንደር እና ሸዋ) ሲስፋፋ የተፈፀመው ጥፋት የታሪክ ጥቁር ነጠብጣብ ኾኖ አልፏል።
አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶች፣ ሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶባቸው ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ተገድለዋል፣ በመቶ ሺዎች ተፈናቅለዋል፤ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ጾታዊ እና አካላዊ ጥቃት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጨምሮ በሌሎች ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሞጋች ድርጅቶች ተመዝግቦ ለዓለም ይፋ ኾኗል።
በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የነበረውን የደም ትስስር እና የጉርብትና እሴት በፖለቲካዊ ሴራ ለመበከል ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።
ከታሪክ ያልተማረው ሕገወጡ የሕወሃት ሥብሥብ በጦርነቱ ከተሸነፈ እና የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላም ቢኾን የሰላሙን መንገድ ወደ ጎን በማለት አሁንም የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል።
ሕገወጡ የሕወሀት ቡድን በአሁኑ ወቅት ሕጻናትን እና ወጣቶችን ከመንገድ እያፈነ ወደ ጦር ካምፕ እያስገባ፣ እናቶችን እያስለቀሰ ይገኛል ።
የትግራይ የሰላም ኀይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር በየነ እንደሚሉት ሕገወጡ ሕወሃት ከሌሎች የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር “ጽምዶ” የተሰኘ የባንዳዎች እና የአኩራፊዎች ሥብሥብ ፈጥሮ ሀገር የማፍረስ እንቅስቃሴ እያደረገ መኾኑን አረጋግጠዋል።
ዛሬም ቢኾን ይህ ሕገ-ወጥ ቡድን የአማራ ክልል ሕዝብ ምስቅልቅል ችግር ውስጥ እንዲገባ አቅዶ እየሠራ ይገኛል።
የአማራ ሕዝብ የትላንት ቁስሉ ሳይደርቅ በሕገወጡ ሕወሃት የፖለቲካ ሴራ እና የውክልና ጦርነት ዛሬም የህልውና አደጋ ተጋርጦበታል። ከዚህ ቀደም የደረሱበትን በደሎች እና አሁንም እየተሸረቡ ያሉትን ሴራዎች በንቃት በመረዳት ሀገራዊ አንድነቱን እና ህልውናውን አስከብሮ ለዘላቂ ሰላም የሚደረገውን ትግል አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleአሚኮ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን በመወጣት ተተኪ ትውልድ ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።