“የባሕር ኃይላችን መልሕቅ የጣለበት፤
የጠቅል አሽከሮች በፓሪስ እና በኒውዮርክ የተሟገቱለት፤
የአሉላ ፈረሶች ውኃ የጠጡበት፤
የኢትዮጵያ ወጣቶች ዋና የዋኙበት፣
የት አለ ባሕሩ በደም የማልንበት?”
ሲል ኢትዮጵያ ከባሕር በር ስትገለል እና የባሕር ኃይሎቿ ሲበተኑ በወቅቱ የባሕር ኃይል አባሉ ተቀኝቷል።
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። ከአሰብ በተጨማሪ ከአዱሊስ እስከ ገምበዛ፤ ከዘይላ እስከ ምፅዋ ድረስ በርካታ ወደቦች ነበሯት። ከአክሱም እስከ ዛግዌ፤ ከአጼ ፋሲል እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ ሙሉ በሙሉ ከባሕር በር ሳትገለል ተጠቃሚ ኾና ቆይታለች።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚነት በዘረኝነት ተጸንሶ፤ በመከፋፈል በተወለደው በሕገ ወጡ ሕወሃት ሊገታ ችሏል። ሕገ ወጡ ሕወሃት ሀገሪቱን በሚያሥተዳድርበት ወቅት የባሕር በር አስፈላጊ እንዳልኾነ በመናገር እና በአልጀርስ ስምምነትን በመፈጸም ኢትዮጵያን ከባሕር በር በማግለል ታሪክ ይቅር የማይለው ጠባሳን ፈጽሟል።
ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ.ር) “አሰብ የማን ናት” በተሰኘው መጽሐፋቸው በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ “አሁን የአሰብንም፣ የምጽዋንም ወደብ አንጠቀምም፤ እነዚህ ወደቦች ባለመጠቀማችን ምንም የቀረብን ነገር የለም” በማለት መናገራቸውን ጽፏል።
ወደብ ባለመኖሩ ረሃብ አይመጣም፣ በጎረቤት ሀገር ወደብ በመጠቀም መሥራት ይቻላል ማለታቸውንም በመጽሐፉ ተቀምጧል። “ኢትዮጵያ ያለወደብ ቀረች ብለን የምንቆጭበት እና የምናዝንበት ምክንያት የለም” ማለታቸውም እንዲሁ። ወደብ አስፈላጊ አይደለም በማለት የወደብ ጠቃሚነትን በወቅቱ አጣጥለዋል።
የወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር “አሰብን ወደ ኢትዮጵያ እንመልስ ማለት ከኢትዮጵያ መንግሥት እምነት እና መርሕ ውጭ ነው፤ አሰብ የምንታገልለት ጉዳይ አይደለም፤ ሌሎች አማራጭ ወደቦች አሉ፤ ስለዚህም ነው በአልጀርስ ድርድር ወቅት አሰብን ያላነሳነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
አሰብን እንይዛለን የሚል አካሄድ ከዘውዳዊ እና ትምክህታዊ አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው በማለትም አጣጥለዋል። ሕገ ወጡ ሕወሃት የአልጀርሱን ስምምነት በመቀበል፣ በሽግግር መንግሥት ኤርትራ ከነወደቦቿ እውቅና እንድታገኝ በማድረግ፤ በድንበር ኮሚሽኑ ክርክር ወቅት አሰብ በኢትዩጵያ ድንበር እንዳትከለል በማድረግ በኢትዮጵያ ታሪክ ይቅር የማይባል በደል መፈጸሙን የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ።
ከመነሻው ብሔርተኝነት እና መከፋፈልን ያነገበው ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ከሥልጣን ከወረደ በኋላም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እየሠራ ይገኛል። የኢትዮጵያ ስኬት እንደ እግር እሳት የሚለበልበው ሕገ ወጡ ሕወሃት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሰለፍ፤ የፕሪቶሪያ ስምምነትን በመጣስ የተለያዩ ትንኮሳዎችን እየፈጸመ ይገኛል።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል፤ የኤርትራ ዜጎች በአምባገነን ሥርዓት እንዲጨቆኑ፤ ዜጎቿ ለስደት እንዲጋለጡ ያደረገው ሕወሃት ማልያውን ቀይሮ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመጣመር ኢትዮጵያን ለማጥፋት እየሠራ ነው።
የእስስትነት ባሕሪው ያለቀቀው፤ መርዙን በምላሱ ይዞ የሚጓዘው ሕገ ወጡ ሕወሃት የትግራይ ወጣቶችን በጦርነት ሊያጠፋ አስገድዶ እያፈነ ይገኛል። የእናቶች የሰላም ተማጽኖ፤ የአባቶች የሰላም ልመና፤ የኢትዮጵያ መንግሥትን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ባለመቀበል የግጭት አባዜውን ብቻ አድምጧል።
ዓለም አቀፍ የፖለቲካ እና የሕግ ምሁሩ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም በአንድ ወቅት ከሕገ ወጡ ሕወሃት
የፕሪቶሪያ ስምምነትን ያለቅድመ ሁኔታ መፈጸም፤ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ችግሮች እንዲፈቱ መፍቀድ፤ ሰላምን በማስቀደም በሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን ማጽናት፤ የትግራይ ሕዝብን ዘላቂ ሰላም ማስቀደም ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ሊወስደው የሚገባ የመፍትሔ ተግባር መኾኑን ተናግረዋል።
የትግራይ ምሁራን የሕገ ወጥ ቡድኑን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በማጋለጥ፤ ሕዝቡን በማንቃት፤ ጦርነትን በማውገዝ ሰላምን ማስቀደም ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
