
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ የሃይማኖት ተቋማት፣ የመንግሥት ተቋማት መሪዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በሰላም ግንባታ እና ግጭት አፈታት ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አማካሪ ኮሎኔል ባምላኩ ዓባይ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን፤ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት እንቅስቃሴዎች ወደተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገሩ፤ በግጭት አፈታት እና ሰላም ግንባታ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑን ገልጸዋል።
በክልሉ አጋጥሞ የነበረውን የሰላም ችግር ለመፍታት የሃይማኖት አባቶች እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከመንግሥት ጋር በመኾን ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ኮሎኔሉ ተናግረዋል። በተለይም በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች ጋር በተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች የሃይማኖት ተቋማት ያነሷቸው የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች በጥናት ተደግፈው አብዛኞቹ ምላሽ ማግኘታቸውን እና የተቀሩትም ወደ ተግባር መግባታቸውን ጠቁመዋል።
የመንግሥት እና የሃይማኖት ተቋማት አንዳቸው በሌላው ጣልቃ ሳይገቡ፣ ነገር ግን በጋራ በሚያሳስቡ እንደ ሰላም ግንባታ እና ግጭት አፈታት ባሉ ሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት እንደሚሠሩ ነው ያነሱት።
ሰላም ለሀገርም ኾነ ለግለሰብ የዕለት ከዕለት ሕይወት መሠረት በመኾኑ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል እና ባለድርሻ አካላት ሰላምን ለማስፈን እና ለማስቀጠል ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙ የሃይማኖት ተቋማት አባቶች እና ሌሎች ተሳታፊዎች ለክልሉ ሰላም አስተማማኝነት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል። በተለይ አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ የሃይማኖት ተከታይ ከመኾኑ አንጻር ማኅበረሰቡ ከማንኛውም አካል በላይ ለሃይማኖት አባቶች ልዩ አክብሮት እና ታዛዥነት እንዳለው ይታመናል ብለዋል።
በመኾኑም ተቋማቱ እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በክልሉ ሰላምን በማስፈን እና ግጭቶችን በመፍታት ሂደት ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
