ተፈጥሮ፣ ታሪክ እና ዘመናዊ ልማት፤ ለባሕር ዳር አዲሱ የቱሪዝም ምዕራፍ

9
🚢
ታሪክ ከተፈጥሮ ጋር በተዋሃዱባት፤ ሁለቱም ሳይሰስቱ ውበት ባደሉባት እና ታሪክ ባጠገቧት ምድር ላይ የቆመችው ውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ በለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለች።
ከተማዋ ከመሐል ሀገር፤ ከሸዋ፣ ከወለጋ፣ እስከ ጎንደር እና ሰሜን ድረስ እንደወርቃማ ድልድይ በማገልገል የብዙ ንግድ መዘዋወሪያ ማዕከል በመኾን ለረጅም ዘመናትም የቆየች ናት።
​ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የባሕር ዳር ደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮኘላን ማረፊያን በመረቁበት ወቅት ታሪካዊቷ ጎርጎራ ከመሀል ሀገር የሚመጡ ሰዎችን ወደ ሰሜን በማሻገር ትልቅ የንግድ ማዕከል እንደነበረች ገልጸዋል። አሁን ታሪክን መለስ ብሎ በመቃኘት የተጀመሩ መልካም ጅማሮዎች ለነገዋ ባሕር ዳር ትልቅ ተስፋን እየዘራ ይገኛልም ብለዋል።
ባሕር ዳር ከተማን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የጎርጎራ ሪዞርት እና በባሕር ዳር የተገነባው ፈለገ ግዮን ሪዞርት መሃል ያለውን ትስስር ለማጠናከር፣ እንደ ጣና ነሽ ያሉ በኢትዮጵያ ትልልቅ የኾኑ መርከቦችን ወደ አካባቢው ማምጣት መቻሉንም አንስተዋል።
ከተማዋ እምቅ የቱሪዝም ሐብት አላት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም ለሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ የድርሻውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ታስቦ መሠራቱን ጠቁመዋል።
በባሕር ዳር እና በጎርጎራ መካከል ባሉ ውብ ደሴቶች ላይ የሚገኙት ታሪክ ጠገብ ቅርሶች ለቱሪስቶች ከፍተኛ ትምህርት የሚሰጡ ሲኾን፣ የትራንስፖርት ሁኔታዎችን በማሻሻል በርካታ ቱሪስቶችን ማዘዋወር የሚያስችል ዕድል የተፈጠረ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከለውጡ በኋላ በክልሉ ብቻ ሳይኾን በከባቢው ጭምር በግዝፈቱ እና በጥራት ትልቅ ዘመናዊ ድልድይ በከተማዋ መገንባቱንም ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተማዋን የበለጠ ውብ በማድረግ የሃብት እንቅስቃሴ ማዕከል እንዲትኾን እያስቻሏት ይገኛሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተገነባ ያለው ግዙፍ ስታዲየም ሲጠናቀቅ ከተማዋ ከሀገር ውስጥም ኾነ ከአፍሪካ የሚመጡ እንግዶችን በድምቀት የምታስተናግድበት ታላቅ መድረክ ይኾናል ነው ያሉት።
በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እና በመንግሥት ቅንጅት በከተማዋ እውን እየኾኑ ያሉት የልማት ሥራዎች፤ የከተማዋን ውበት፤ ታሪክ እና መልካም ማኅበረሰብ የተዋሃዱባት እና ወደዚች ከተማ የሚመጡ እንግዶች በፍጹም የማይቆጩባት የብልጽግና ተምሳሌት ልትኾን እንደምትችል ነው ያመላከቱት።
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሳይበር ጥቃቶች በታዳጊዎች ላይ እየበዙ ነው!
Next articleየመንግሥት እና የሃይማኖት ተቋማት ቅንጅት ለሰላም ግንባታ እና ግጭት አፈታት !