
ቀደምት ኢትዮጵያውያን በጎ ነገርን የሚያውክ ወይም የሚበክል ሰው ባለበት ኹሉ ሰላም እና ስምምነትን ማምጣት ከባድ መኾኑን ለማስገንዘብ “በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል” በማለት ከአጥፊ ሰዎች መራቅ ለሰላም እና ለስምምነት ወሳኝ መኾኑን ያስገነዝባሉ።
አባባሉ የኢትዮጵያውያን የኾነ፤ ኢትዮጵያንም በአግባቡ የሚገልጻት ኾኖ አናገኘዋለን። ሰላም እና አንድነቷን አስጠብቃ ወደ ኹለንተናዊ ዕድገት ለመሻገር በምታደርገው የረጅም ዓመታት ጉዞዋ መንገዷ ላይ የሚቆሙ ደንቀራዎች አያጧትም።
እነዚህ ታሪካዊ ፈተናዎች ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ከመቀጠል ባያግዷትም ሰላሟን በማደፍረስ፣ አንድነቷን በማናጋት እና የኢኮኖሚ ዕድገቷን ወደ ኋላ በመጎተት በሚገባት ልክ እንዳታድግ ሲያደርጓት ለዘመናት ዘልቀዋል። ከፍተኛ ዋጋም አስከፍለዋታል።
እነዚህ እንቅፋቶች መልክ እና ስልታቸውን ከጊዜው ጋር እያቀያየሩ እና እያመሳሰሉ ኢትዮጵያ የምታድግ በመሰላቸው ጊዜ የሚከሰቱት ናቸው። በአሁን ወቅትም ዘላቂ ሰላሟን እና ኹለንተናዊ ዕድገቷን እንደሚያረጋግጥ ከፍተኛ እምነት የተጣለበትን የብሔራዊ ምክክር ጉባኤ ጥላሸት ለመቀባት እየጣሩ ይገኛሉ።
በምክክሩ ሂደት መግባባት ላይ ለመድረስ የሚደረጉ ጭቅጭቆችን እና ክርክሮችን እንደ ውድቀት አድርገው በማሰራጨት በሕዝቡ ዘንድ ተስፋ መቁረጥን እና አለመተማመንን ለመዝራት ቀን ከሌሊት ሲታትሩ እየተመለከትን እንገኛለን።
እውነታው ግን ወዲህ ነው። የፖለቲካ ሳይንስ እና የሰላም ግንባታ ምሁራን እንደሚሉት ሀገራዊ ምክክር ማለት ኹሉም ሰው አስቀድሞ በተስማማበት ሀሳብ ላይ አጨብጭቦ የሚወጣበት መድረክ አይደለም። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ጠርዝ የያዙ ታሪካዊና መዋቅራዊ ጥያቄዎች ባሏቸው ሀገራት በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተመካካሪዎች የሚያደርጉት ከፍተኛ የሀሳብ ፍትጊያ እና ጭቅጭቅ የምክክር ሂደቱ እውነተኛ መኾኑን የሚያሳዩ መኾናቸውን ያረጋግጣሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በተደጋጋሚ እንደገለጹትም የምክክር ጉባኤው የበርካታ ማኅበረሰብ ክፍሎችን ሀሳብ እና ጥያቄ ያስተናገደ ታሪካዊ መድረክ በመኾኑ በጉባኤው ላይ የሀሳብ ፍጭቶች እና ጭቅጭቆች መኖራቸው የሚጠበቅ ነው። የዴሞክራሲያዊ ሂደት አንዱ መገለጫ ተደርጎም ይወሰዳል ብለዋል።
እውነተኛ ሰላም እና መግባባት የሚመጣው ቅሬታዎች እና ልዩነቶች ሳይሸሸጉ እና ሳይድበሰበሱ አደባባይ ወጥተው በሃሳብ ሲሞገቱ እና አሳማኝ መፍትሔ ሲፈለግላቸው መኾኑም ይታመናል።
ታላላቅ ሀገራዊ ችግሮች በአንድ ጀምበር አይፈቱም። የምክክሩ ሂደት በራሱ የውጤቱን ያህል ትልቅ ዋጋ እንዳለው ይታመናል። የታሪክ እና የማኅበረሰብ ጥናት ምሁራን እንደሚገልጹት ስኬታማ የኾኑ ብሔራዊ ምክክሮች በሂደት መተማመንን በመገንባት ለትውልድ የሚሻገር እና በየጊዜው የሚያጋጥሙ ሀገራዊ እና ማኅበረሰባዊ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት አዲስ የፖለቲካ ባሕልን የሚቀርጹ ናቸው። ኢትዮጵያ የጀመረችው ብሔራዊ የምክክር ጉባኤም በዚህ ልክ ዓላማ ያለው ነው።
ስለኾነም ከጉባኤው መልካም ፍሬን የሚጠብቁት ኢትዮጵያውያን በጥባጮችን ተው በማለት፤ ለሀሰተኛ መረጃዎቻቸው ጆሮ ባለመስጠት፤ የበጥባጮችን እና የሴረኞችን አሉታዊ ፕሮፓጋንዳ በንቃት በመከላከል የምክክር ጉባኤው የሚደርስባቸውን የመጨረሻ ውሳኔዎች በትዕግስት መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
በርግጥም ኢትዮጵያ ያቀደችውን ታላቅ ርዕይ እውን በማድረግ ወደ ተሻለ ዕድገት ትሻገር ዘንድ መሰል የሀሰተኛ መረጃ መርዞችን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ያስፈልጋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
