
የአማራ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየብስ፣ በአየር እና በውኃ ትራንስፖርት እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ክልሉን በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ መስተጋብር በከፍተኛ ደረጃ ከማሳደግ ባለፈ ከትራንስፖርት ተደራሽነት ጋር በተገናኘ ከዚህ ቀደም ለዘመናት ሲነሱ ለነበሩ የሕዝብ ጥያቄዎች ተጨባጭ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው።
በክልሉ የየብስ ትራንስፖርት ዘርፍ አዳዲስ መንገዶችን ከመገንባት ጀምሮ የአገልግሎት አሰጣጥን እስከማዘመን ድረስ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ክልሉን ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም የክልሉን ዞኖች እርስ በዕርስ የሚያስተሳስሩ ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት በክልሉ የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እና የክልሉን የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ እየተሠራ ያለው ሥራ በጥሩ የሚነሳ መኾኑን ጠቁመዋል። ከሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር ሳይዘል የኖረውን የመንገድ ሽፋን ወደ 4 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር ማድረስ መቻሉንም ጠቁመዋል። 61 የመንገድ ፕሮጀክቶች በመሠራት ላይ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። የአዲሱ የዓባይ ድልድይም የዚሁ ስኬት አካል ነው።
የትራንስፖርት አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግ በተለያዩ ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ መናኸሪያዎች እየተገነቡ እና ተደራሽነታቸውም እያደገ መጥቷል። በባሕር ዳር፣ ደብረ ብርሐን፣ ደሴ እና በሌሎችም ዋና ዋና ከተሞች የተጀመረው የዲጂታል ቲኬት አገልግሎት (ኢ-ቲኬቲንግ) ሥርዓት በዘርፉ ትልቅ አብዮት ፈጥሯል። ይህም መንገደኞች ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ፣ የትራንስፖርት ስምሪት ሥርዓቱ ግልጽ እንዲኾን፣ ከሕገ-ወጥ ደላሎች እና ከዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ የነበረውን እንግልት በማስቀረት አገልግሎቱን በከፍተኛ ሁኔታ አዘምኖታል።
የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታም ዳግም መጀመሩ ክልሉ በምጣኔ ሀብት እና በልማት ያለውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ አጋዥ የሚኾኑ ናቸው።
የአየር ትራንስፖርት ዘርፉም በክልሉ የፈጠረው መነቃቃት የኢኮኖሚውን እና የቱሪዝሙን አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል። በቅርቡ ተገንብቶ ሥራ የጀመረው የደብረ ማርቆሱ የንጉስ ተክለሃይማኖት አየር ማረፊያ የአካባቢው ሕዝብ ለረጅም ጊዜ ሲያነሳው ለነበረው የመልማት ጥያቄ ታሪካዊ ምላሽ የሰጠ ነው። ከዚህም ባሻገር እንደ ጮቄ ተራራ ያሉ እምቅ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ በጎጃም አካባቢ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የኢንቨስትመንት መነቃቃት ይፈጥራል፤ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ቱሪስቶችም ሰፊ ዕድል ይከፍታል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቀጥሎ ትልቅ እና ዘመናዊው የተርሚናል ግንባታ የተካሄደለት የባሕር ዳሩ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ አየር ማረፊያ የትራንስፖርት ዘርፉ ማደግ ሌላው ማሳያ ነው። ይህ ዘመናዊ ተርሚናል የባሕር ዳር ከተማን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም እና የኮንፈረንስ ማዕከልነት ጉዞ በእጅጉ ያፋጥናል።
በውኃ ትራንስፖርት ዘርፍ በተለይም በጣና ሐይቅ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገሩት ነው። ባሕላዊ የውኃ ላይ ጉዞዎችን እና አደጋን ሊያስከትሉ የሚችሉ የትራንስፖርት መስመሮችን በመተካት ዘመናዊ እና ደኅንነታቸው የተጠበቁ ጀልባዎች ወደ ሥራ መግባታቸው የውኃ ላይ ትራንስፖርቱን ምቹ፣ ቀልጣፋ እና አስተማማኝ አድርጎታል።
የውኃ ትራንስፖርቱ ዕድገት ከቱሪዝም ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው። በተለይም በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተገነባው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ለውኃ ትራንስፖርቱ የላቀ ትርጉም ሰጥቶታል። ከባሕር ዳር እስከ ጎርጎራ የሚዘረጋው የውኃ ላይ ጉዞ መስመር ቱሪስቶች የጣና ሐይቅ ገዳማትን እና የተፈጥሮ ውበትን እያጣጣሙ እንዲጓዙ ከማድረጉም በላይ ሪዞርቶቹን እርስ በዕርስ በማስተሳሰር የአካባቢውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ እንዲነቃቃ አግዟል።
በአጠቃላይ የአማራ ክልል በየብስ፣ በአየር እና በውኃ ትራንስፖርት ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶች የሕዝቡን የዘመናት ጥያቄ ከመመለስ ባሻገር ክልሉን የሀገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የንግድ እና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ሰፊ በር ከፍቷል። እነዚህ ስኬቶች ክልሉ በሁሉም መስክ ለሚያደርገው የዕድገት ጉዞ የማይተካ ሞተር ኾነው ይቀጥላሉ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
