“ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

6

 

የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ሌሎችም መሪዎች በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል። ክልሉ በችግር ውስጥም ኾኖ ሰፊ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በተለይም በግብርና ልማት ማሻሻያ ላይ ያተኮሩ ሥራዎች በሰፊው ተከናውነዋል ነው ያሉት። ለዘመናት ሲጓተቱ የቆዩ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እየተከናወኑ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

የቱሪዝም ዘርፉን የሚያነቃቁ ታላላቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች መገንባታቸውንም ጠቅሰዋል። የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት እና የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በቅርቡ ከተገነቡት የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል ስለመኾናቸው በአብነት አንስተዋል።

ከተሞች ለነዋሪዎች የተመቹ እንዲኾኑ የሚያደርጉ አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አንስተዋል። በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ እና በወልድያ ተስፋ ሰጭ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋልም ነው ያሉት።

ከደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናል በተጨማሪ ቀደም ሲል በደብረ ማርቆስ እና ኮምቦልቻ የተገነቡት የአውሮፕላን ማረፊያዎች የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት መግቢያ መስኮቶች ኾነዋል ብለዋል።

በክልሉ እየተገነቡ ላሉት ፕሮጀክቶች እና የልማት ሥራዎች በቅርበት እየደገፉ ላሉት የፌዴራል መንግሥት መሪዎች ርእሰ መሥተዳድሩ ምሥጋና አቅርበዋል።

#AMECO #BahirDarAirport #EthiopiaInfrastructure #EthiopianAirlines

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_30_2018_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ መልእክት፦